Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ለጥሩነሽ ቤጅንግ ሆስፒታል የሕክምና ግብዓት ድጋፍ ልታደርግ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና መንግሥት ለጥሩነሽ ቤጅንግ ሆስፒታል 8 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ሚያወጣ የሕክምና ግብዓት ድጋፍ ሊያደርግ ነው፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በቻይና ብሄራዊ ጤና ኮሚሽን ምክትል ሚኒስትር ዶክተር ካኦ ዡታዎ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ባሉ ትብብሮች እና ለቀጣይ በጋራ ሊሠሩ በሚችሉ የጤና ሥራዎች ላይ መክረዋል፡፡

ዶክተር ሊያ በውይይ ላይ እንደገለጹት÷ የቻይናመንግሥት ለጥሩነሽ ቤጅንግ ሆስፒታል በሚያርገው ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው፡፡

የድንገተኛ ሕክምናና የአደጋ ምላሽ አሰጣጥን ለማሳደግና ቴሌ ሜድስንን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተም ልምድ ለመለዋወጥ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

ተጨማሪ መድኅኒት አምራች ባለኃብቶችም በኢትዮጵያ እንዲሠማሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ዶክተር ካኦ ዡታዎ በበኩላቸው÷ ጥሩነሽ ቤጅንግ ሆስፒታል በቻይና መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው ድጋፉ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም መንግሥታቸው በአዳዲስ ቴክኖሎጅዎችና ስፔሻሊቲ ሕክምናዎች ላይ በተለይም በቻይና ባህላዊ ሕክምና ዙሪያ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል፡፡

ቻይና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በቅድመ ምርመራ ላይ እየሠራች መሆኗን ገልፀው÷ ቀላልና አስተማማኝ የቴክኖሎጅ ውጤቶች መኖራቸውንና በዚህም ዙሪያ በትብብር እንሠራለን ብለዋል፡፡

ከውይይታቸው በኋላም÷ የቻይና መንግሥት ለጥሩነሽ ቤጅንግ ሆስፒታል የ8 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሕክምና ግብዓት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከጤና ሚኒስቴር ጋር ፈርሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.