Fana: At a Speed of Life!

የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ “ተጨባጭ እና ተግባራዊ” ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን እንዲያዘጋጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 17ኛው የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ “ተጨባጭ እና ተግባራዊ” ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን እንዲያዘጋጅ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠየቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ እያስተናገደች ባለችው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸው የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ከ17ኛው ኢንተርኔት አስተዳደር ጉባዔ አምስቱ ንኡስ መሪ ሃሳቦች ጋር በተጣጣመ ቁልፍ የዕድገት ጉዞዎች የታጀበ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ሽፋን በፈረንጆቹ 2017 ከነበረው 19 ሚሊየን ተጠቃሚዎች በ2022 ወደ 30 ሚሊየን ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል፡፡

የ4ጂ ኔትወርክ ህዝብ በሚበዛባቸው ከተሞች እና 5ጂ ኔትወርክን በትላልቅ ከተሞች መዘርጋቱ ግንኙነቱን እያፋጠነ ነው ብለዋል።

በመላ ሀገሪቱ 2 ሺህ300 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፥ ያለፉት አራት ዓመታት ለኢትዮጵያ የፈተናም የእድልም ዓመታት ነበሩ ብለዋል።

ኢንተርኔት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ሀሰተኛ መረጃን ለማሰራጨት መዋሉን በተግዳሮት አንስተዋል፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ደግሞ መንግስት እና የንግድ ተቋማት አገልግሎታቸውን በኦንላይ እንዲሰጡ በማስቻል አዳዲስ ፈጠራዎች እንዲበረታቱ ማድረጉን ያመጣው እድል ሲሉ ዘርዝረዋል።

እንደ አዳጊ ሀገር ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና በምታደርገው ጉዞ ኢንተርኔት መልካም እድል እንደሚፈጥርላት እውቅና እንደምትሰጥም ነው ያመለከቱት።

ከሁለት አመት በፊት ኢትዮጵያ ወደ አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ በምታደርገው ጉዞ አንድ ወጥ የሆነ ራዕይ ያስቀመጠ ብሄራዊ ዲጂታል ስትራቴጂ በስራ ላይ ማዋሏንም አንስተዋል።

ስትራቴጂው መሠረተ ልማትን ማጎልበት፣ ስርዓቶችን ማስቻል፣ ዲጂታል መድረኮችን እና የዲጂታል ስነ-ምህዳርን በመገንባት ላይ ያተኩራል ነው ያሉት።

ደህንነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት መንግስት ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ተቋማትን ለማጠናከር የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷልም ነው ያሉት።

እነዚህ ተቋማት የአገሪቱን የሳይበር ምህዳር ከመጠበቅ በተጨማሪ በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የዜጎችን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጥቅሞችን ተገንዝቦ አዲሱን ቴክኖሎጂ ለሀገራዊ ልማት ስራዎች ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር ግንኙኘት ያላቸውን የምርምርና ልማት ሥራዎችን የሚሰሩ ተቋማት አቋቁመናል ሲሉም በመድረኩ ተናግረዋል።

እንዲሁም በአገልግሎቶች፣ ምርቶች እና መፍትሄዎች ልማት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም እና ተወዳዳሪነት ላይ ለመስራት ቁርጠኛ የሆነ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መቋቋሙንም ነው የገለፁት፡፡

በዚህም ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት በጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ ትራንስፖርት እንዲሁም በህዝብ ጥበቃና ደህንነት ላይ በተለያዩ ዘርፎች እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ሀገራት ከዕሴቶቻችን ጋር በሚስማማ መልኩ እና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ውስጥ እንድንሳተፍ በሚያስችለን ደረጃ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አለብን ብለዋል።

ለዚህም ነው ትኩረትን በሳይበር ምህዳር እምነት፣ ፍትሃዊነት እና ደህንነት መገንባት ላይ መሆን አለበት የምንለው ሲሉም ገልፀዋል ።

በዚህም የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባኤ የተመሰረተው የኢንተርኔትን ዘላቂነት፣ ደህንነት፣ መረጋጋት እና ልማት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ለውይይት መንገድ ለመክፈት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.