Fana: At a Speed of Life!

የሽረ ኮር ሳይት ጥገና ሲጠናቀቅ በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የቴሌኮም አገልግሎት እንደሚያገኙ ኢትዮ ቴሌኮም ገለፀ

አዲስ አበበ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽረ ኮር ሳይት ጥገና ሲጠናቅ በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የቴሌኮም አገልግሎት እንደሚያገኙ ኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናገሩ፡፡

ስራ አስፈፃሚዋ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረባው ጦርነት ምን ያህል ውድመት እንደደረሰ ለማወቅ ዳሰሳ እንደሚስፈልግ ተናግረው፥ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ግን መግባት እስከተቻለባቸው አካባቢዎች የጥገና ሰራተኞቻችን ተልከዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ቀደም ብሎ ጥገና ማድረግ የሚስችለንን ዝግጅት ሲደረግ በመቆየቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሙሉ አቅም ባይሆንም አገልግሎት ማስጀመር መቻሉን ተናግረዋል።

ለዚህም ማይፀብሪ፣ አላማጣ፣ ኮረም እና ዓዲ ሓቂ ከተሞችን ያነሱ ሲሆን፥ በአካባቢዎቹ በተለይ በሞባይል አማካኝነት በድምፅ የሚገናኙበት እድል ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሽረ የሚገኘውን ኮር ሳይት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችል ቅኝት ተደርጓል፤ ሳይቱ ለሁለት ዓመት አግልግሎት ሳይሰጥ እንደመቆየቱ የጎደሉ እቃዎችን ማሟላትን ጨምሮ ሌሎች ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

በርብርብ በተከናወነ ስራም 266 ኪሎ ሜትር የፋይበር ጥገና ማከናወን መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ጥገናውን ለማጠናቀቅ 6 ኪሎ ሜትር ይቀረናል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፥ የጥገና ስራው ሲጠናቀቅም ከአስቸኳይ የቴሌኮም አገልግሎት በዘለለ ሰፊው ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል፡፡

ከሽረ ቀጥሎ አክሱም እና አድዋም አገልግሎት እንዲያገኙ የማስተላለፊያ መስመር ፍተሻ ጀምረናል ያሉ ሲሆን፥ በቅርቡም በርካታ ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.