በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሞተ አንድም ሰው የለም- የጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሞተ አንድም ሰው እንደሌለ እና ህብርተሰቡ ራሱን ከሀሰተኛ ዜናዎች መጠበቅ እንዳለበት የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
አሁን ላይ በአለማችንም ሆነ በአገራችን ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ባልተናነሰ ፍጹም ከእውነት የራቁና ምንጫቸው ያልታወቁ የሀሰት መረጃዎች በማህበራዊ የትስስር ገጾች እየተለቀቁ መሆኑን ሚኒስቴሩ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የተሳሳተ መረጃን መልቀቅም ሆነ ተቀብሎ ማሰራጨት ከተፈጠረው ቀውሱ እኩል ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ችግሮችን ያስተከትላልም ነው ያለው።
በመሆኑም ይህ አይነት እኩይ፣ ኢ-ሞራላዊና ህገ ወጥ ድርጊትን ሁሉም በጥብቅ ሊያወገዘውና ሊከላከለው ይገባል።
ይህን የሀሰት መረጃ በማመን ህብረተሰቡ እንዳይደናገጥና እንዳይደናገር በማሳሰብም መረጃዎችን በማዛባት የሚያሰራጩ ኃላፊነት የጎደላቸውን ግለሰቦችና ቡድኖችንም በማጋለጥና ለህገ በማቅብ በጋራ መከላከል ይገባናል ብሏል፡፡
ኮቪድ-19ን በተመለከተ መንግስት ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን በማደራጀት በየዕለቱ የማሠራጨት ሥራን እያከናወነ መሆኑንም አስታውቋል።
ስለሆነም ማህበረሰቡ ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃ በመከተል እና በመጠቀም በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በተረጋጋ አካሄድ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርቧል፡፡