Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ባንክ ለአደጋ ተጋላጭ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ745 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ ለአደጋ ተጋላጭ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ745 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ በኢትዮጵያ ያለውን የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎትን እና የጎርፍ አስተዳደር ፕሮጄክትን ለመደገፍ የሚውል ድጋፍ አጽድቋል።

ድጋፉ በጤናው ዘርፍ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርአት ለማሻሻል እና የተቀናጀ የጎርፍ አስተዳደር ሥርአትን ለመዘርጋት የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን የሚቋቋም አቅምን ለመገንባትና ብሎም የአደጋ ጊዜ እና የጎርፍ አደጋዎችን ለመቆጣጠር የሚያግዝ መሆኑም ነው የተገለጸው።

የተደረገው ድጋፍ ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር እና በዓለም ባንክ የብድር አመቻች ክፍል የተገኘ ሲሆን፥ ለጤናው ዘርፍ ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር 400 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም አመቻች ክፍሉ 45 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል።

ከዚህ ባለፈም ለተቀናጀ የጎርፍ አስተዳደር ሥርአት የሚውለው 300 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር የተገኘ ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል።

ለጤናው ዘርፍ በተደረገው 445 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ በአብዛኛው በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሆኑ ከ22 ሚሊየን በላይ ሴቶችና ህጻናት ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው የተባለው።

በዋናነትም በሶስተኛ ወገን የሚተገበርና ወሳኝ እና ተደራሽ የጤና አገልግሎትን ማዳረስን አላማው ያደረገ ሲሆን፥ የእናቶችና ህጻናት ጤና ክብካቤን ማሻሻል እና የተመጣጠነ ሥርአተ ምግብን ማስፋፋትን አላማው ያደረገ ነው ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ክትባትን ተደራሽ ማድረግ፣ የቤተሰብ እቅድን መተግበር፣ አዋላጅ የህክምና ባለሙያዎችን ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ፣ የቅድመ እና ድህረ ወሊድ የህክምና ክትትልን ለመደገፍ የሚውል መሆኑንም በአፍሪካ ቀንድ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ዑስማን ዲዮን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በግጭት ምክንያት የወደሙ የጤና መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን በድጋሚ እንዲያገኙ ለማስቻል ያለመ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በ300 ሚሊየን ዶላር የሚተገበረው የተቀናጀ የጎርፍ አስተዳደር ስርአት በዋናነት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የሚቋቋም አቅምን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑም ነው የተገለጸው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለአደጋ ጊዜ እና የጎርፍ ስጋቶችን ለመቋቋም የምትሰጠውን ምላሽ የማሳደግ አላማ አለው ነው የተባለው።

ይህ ፕሮጄክት በዋናነት የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ስጋቶችን፣ የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት አስተዳደር እና የከፋ የጎርፍ ተጋላጭነት ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚተገበረውን የተጋላጭነት ቅነሳ በዋናነት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የባንኩ መረጃ ያመላክታል።

በዚህ ፕሮጄክትም ወደ 34 ሚሊየን የሚጠጉና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ በአዋሽ እና ኦሞ ተፋሰስ እንዲሁም ሪፍት ቫሊ ሐይቅ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች በቅድሚያ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.