አክሱምና አድዋ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት አገኙ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለረጅም ጊዜ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸው የቆዩት አክሱም፣ አድዋና ውቅሮ ማሪያም ከተሞች በዛሬ ዕለት ዳግም አገልግሎቱን አግኝተዋል፡፡
እነዚህ ከተሞች ዳግም ተጠቃሚ የሆኑት ከሽረ-አድዋ የተዘረጋውን የ66 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር እንዲሁም የመካከለኛ የዝቅተኛ መስመር የጥገና ሥራ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው፡፡
ተቋማችን በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት በኤሌክትሪክ ማሰራጫ መሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ከስር ከስር መልሶ በመጠገን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸውን አካባቢዎችን ዳግም ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ይታወቃል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም ከአማራና አፋር ክልል በተጨማሪ በትግራይ ክልል የቴክኒክ ባለሞያዎችን በማሰማራትና አስፈላጊ ግብዓቶችን በሟሟላት አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎችን ዳግም ተጠቃሚ እየተደረጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አሁንም በሶስቱም ክልሎች ቀሪ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያላገኙ አካባቢዎችን ዳግም ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡