Fana: At a Speed of Life!

የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች በንጹህ የመጠጥ ውኃ እጥረት መቸገራቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች “የንጹህ መጠጥ ውኃ በምንፈልገው ልክ እየቀረበልን አይደለም” ሲሉ ገለጹ፡፡

ቅሬታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች÷ “እንደ አካባቢው ሊለያይ ቢችልም በአማካይ ከሁለት ሣምንት እስከ ሁለት ወር ድረስ ውኃ የማናገኝበት ጊዜ አለ” ይላሉ፡፡

ይህም ከሠርካዊ እንቅስቃሴያቸው በተጨማሪ በማህበራዊ ዝግጅቶች ላይ ዕክል እንደፈጠረባቸው ነው የሚናገሩት፡፡

ለ20 ሊትር ውኃ በአማካይ የውኃውን ግዥ እና የማጓጓዣውን ጨምሮ ከ15 እስከ 20 ብር እንደሚያወጡ ገልጸዋል፡፡

እንደ ከተማ እየቀረበ ያለው ንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እና የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር አለመጣጣሙን የጠቆሙት አስተያየት ሰጭዎቹ÷ ያለውን ውኃ በፍትሐዊነት የማዳረስ ችግር መኖሩንም አንስተዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ውኃ መስኖና ማዕድን ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍስሐ ዳምጠው የቀረበውን ቅሬታ ትክክለኛነት ገልጸው÷ ችግሩን ለመቅረፍ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጊዜያዊነት ተጨማሪ የውኃ አማራጭ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ÷ ከጣጤሳ አካባቢ በአጠቃላይ 34 ሊትር ፐር ሰከንድ ማመንጨት የሚችሉ ሁለት ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች የሲቪል እና የመካኒካል ሥራቸው ተጠናቆ የመስመር ፍተሻ ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ክፍት ስለሚሆኑ የውኃ አቅርቦት ችግሩን ያቃልሉታል ነው ያሉት፡፡

ከሬቦ ወንዝም 10 ሊትር ፐር ሰከንድ ምርት እየቀረበ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በዘላቂነት ችግሩን ለመቅረፍ ደግሞ ለ20 ዓመታት አገልግሎት የሚሰጥ ስምንት ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶችን ያካተተ እና ከ100 ሊትር ፐር ሰከንድ በላይ ውኃ የሚያመርቱ ፕሮጀክቶች እደሚገነቡ ጠቁመዋል፡፡
የዲዛይን ሥራው ተጠናቆ በጀቱን ለሚሸፍነው ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መላኩን እና ወደ ተግባር ለመግባት የፌደራልመንግሥት ይሁንታ እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪምአሁን ከቦዠባር የሚገኘውን 90 ሊትር ፐር ሰከንድ የውኃ ምርት ወደ 150 ሊትር ፐር ሰከንድ በማሳደግ ተጨማሪ 60 ሊትር ፐር ሰከንድ ለማግኘት መታቀዱን ነው የገለጹት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.