Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እያዘጋጁ ሲሸጡ የነበሩ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እያዘጋጁ ሲሸጡ የነበሩ 3 ግለሰቦች በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
 
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ አካባቢ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
ተጠርጣሪዎቹ ለዚሁ ህገ-ወጥ ተግባር ማስፈፀሚያ የሚውሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክ/ ከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር ጽ/ቤት እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የቀበሌ 01 አስተዳደር ጽ/ቤት የሚሉ ሃሰተኛ ክብ ማህተሞችን እንዲሁም የግለሰብ የስም ቲተር በማስቀርፅ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርማ ያረፈበትን የመታወቂያ ወረቀት አመሳስለው በማሳተም ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
 
ማህተሞቹንና ወረቀቶቹን በአንድ የሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ደብቀው በማስቀመጥ የነዋሪነት መታወቂያ ለሚፈልጉ ሰዎች ሃሰተኛ መታወቂያዎችን እያዘጋጁ እንደሚሸጡ ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ክትትል 3 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
 
ሃሰተኛ መታወቂያውን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው ወረቀቶችና ማህተሞችም ከተደበቁበት በብርበራ እንደተገኙም የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም የተለያዩ ሃሰተኛ ሰነዶችን እያዘጋጁ ለህብረተሰቡ የሚያሰራጩና ህዝቡን ለተለያዩ ጉዳቶች የሚዳርጉ ግለሰቦች በህግ አግባብ እንዲጠየቁ ለማድረግ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
 
የአዲስ አበባ ፖሊስ ሀሰተኛ ሰነድ በመገልገል ጥቅም ለማግኘት የሚሞክሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚቀርቡ ሰነዶችን ህጋዊነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.