Fana: At a Speed of Life!

የእግር ኳስ ከዋክብት በፔሌ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም እግር ኳስ ከዋክብት በብራዚላዊው የምንጊዜም ኮከብ ፔሌ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን እየገለፁ ነው፡፡

የቀድሞዎቹ የብራዚል ከዋክብት ሮናልዶ ሉዊስ ናዛሪዮ ዴሊማ እና ሮናልዲንሆ ጎቾ በእግር ኳሱ ኮከብ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።

እንግሊዛዊው ጋሪ ሊንከርን ጨምሮ የቀድሞ ከዋክብቶች በፔሌ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ታላቅነቱን አወድሰዋል።

ሊንከር “መለኮታዊው የእግር ኳስ ተጫዋች አርፏል፤ ጥቂቶች በሚመረጡበት እግር ኳስ 3 ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያነሳው ፔሌ ቢሊየንም በእግር ኳሱ ግን ሁሌም ህያው ነው” ብሏል።

ሮቢን ቫንፐርሲ በተመሳሳይ እግር ኳስ ኮከቧን አጥታለች፤ ፔሌ ላደረግኸው ነገር ሁሉ እናመሰግንሃለን ነፍስህ በሰላም ትረፍ ብሏል፡፡

አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ “ካንተ በኋላ በእግር ኳስ መፈጠር ምን ያህል መታደል ነው፤ የእግር  ኳስ ጥበብህ ለእያንዳንዱ እግር ኳስ ተጫዋች ትምህርት ቤት ሆኖ ይቀጥላል” ሲል ስሜቱን ገልጿል።

ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በፔሌ ሞት እግር ኳስ አዝናለች ፔሌ ለሚሊየኖች እግር ኳስ ተጫዋቾች መነሳሳት ምክንያት ነበር ሲል በኢንስታግራም ገጹ መልዕክት አስተላልፏል።

ፔሌ በእያንዳንዱ እግር ኳስ አፍቃሪ ልብ  ውስጥ ይኖራል ያለው ሮናልዶ ለቤተሰቡ እና ለመላው ብራዚላውያን መፅናናትን ተመኝቷል፡፡

ብራዚላዊው ኮኮብ ኔይማር በበኩሉ 10 ቁጥር ከፔሌ በፊት ቁጥር ብቻ ነበር፤ ምስጋና ለንጉሱ ይግባና እግር ኳስና ፔሌ ደረጃቸውን ከፍ አድርገዋል ሲልም ነው ስሜቱን የገለጸው።

ኪሊያን ምባፔ በተመሳሳይ በፔሌ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን የገለፀ ሲሆን  የእግር ኳስ ንጉሱ ጥሎን ቢሄድም ህያው ስራዎቹ ግን ሁልጊዜም አብረውን ይኖራሉ ብሏል፡፡

በክለብ ደረጃ ሪያል ማድሪድ፣ ሊቨርፑል፣ ባርሴሎና፣ ማንቼስተር ዩናይትድ በብራዚላዊው ኮከብ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል፡፡

ከእግር ኳስ ቤተሰቡ  በተጨማሪ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የቀድመው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፣ የአርጀንቲናው ፕሬዚዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ እና የሜክሲኮው ፕሬዚዳንት በፔሌ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል፡፡

በሙሉ የመዝገብ ስሙ ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሚንቶ ወይም በገነነበት የእግር ኳስ ዓለም ፔሌ በክለብ ደረጃ በሀገሩ ክለብ ሳንቶስ እጅግ ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል።

በቆይታውም የሊግ ውድድርን ጨምሮ የደቡብ አሜሪካውያን የክለብ ሻምፒዮናን ኮፓ ሊበርታዶሬስን እንዲሁም የዓለም የክለቦች ዋንጫን አሸንፏል።

በ643 ጎሎችም የሳንቶስ የምንጊዜም ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሲሆን የመጨረሻ የክለብ ተሳትፎውን በአሜሪካው ኒውዮርክ ኮስሞስ በማድረግ የእግር ኳስ ህይወቱን አጠናቋል።

ከሀገሩ ብራዚል ጋርም በአራት የዓለም ዋንጫዎች ተሳትፎ ሶስት ጊዜ የዓለም ዋንጫን በማንሳት ብቸኛው ባለ ታሪክ ነው።

ፔሌ በ19 58፣ 19 62 እና 19 70 የዓለም ዋንጫዎች አሸናፊ መሆን ሲችል፥ በ77 ጎሎችም ከፒ ኤስ ጂው ኮከብ ኔይማር ጋር የብራዚል የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.