Fana: At a Speed of Life!

ፊፋ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን በአለም ዋንጫ ስላሳየው ያልተገባ ባህሪ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ባለፈው ወር በኳታር በተካሄደው የአለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ፥ የ2018 ዓለም ዋንጫ አሸናፊዋን ፈረንሳይን በፍፁም ቅጣት ምት አሸንፋ ዋንጫውን ለሶስተኛ ጊዜ ባነሳችው በአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን “ያልተገባ ባህሪ” ላይ የዲሲፕሊን ሂደቶችን ከፍቻለሁ ብሏል።

በፍፃሜ ጨዋታው መጨረሻ ግብ ጠባቂው ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ በምርጥ በረኛነት ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ ያልተገባ ምልክት ማሳየቱ የተገለፀ ሲሆን፤ ከመቀረጹ በፊት በመልበሻ ክፍል ውስጥ በፈረንሳዊው ኮከብ ኪሊያን ምባፔ ላይ ሲያላግጥ እንደነበር ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪም ማርቲኔዝ በቦነስ አይረስ በተዘጋጀው የድል ሰልፍ በህፃን አሻንጉሊት ላይ የምባፔን ፊት ለጥፎ በተጫዋቹ ላይ በማሾፉ ከበርካቶች ከፍተኛ ትችት ደርሶበታል፡፡

ፊፋ÷ አርጀንቲና “ተጫዋቾችን እና ባለስልጣናትን ባለማክበር እንዲሁም የፍትሃዊ ጨዋታ መርሆዎችን በመተላለፍ ያልተገባ ባህሪ በማሳየት ህግ ጥሳለች ሲል ገልጿል።

በተጨማሪም የአርጀንቲና እግር ኳስ ማህበር የሚዲያ እና የግብይት ህግን በመጣስ ጉዳይ ምርመራ እያካሄደ ስለመሆኑ ማስታወቁን የአልጄዚራ ዘገባ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.