Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ለ4 ሺህ 401 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ4 ሺህ 401 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል ለታራሚዎቹ  ይቅርታ ያደረገው  በይቅርታ ቦርዱ ተመርምሮ መስፈርቱን አሟልተው በመገኘታቸው የክልሉ ምክር ቤት ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በክልሉ ፍትሕ ቢሮ አቅራቢነት በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የሕግ ታራሚዎችን በይቅርታ እንዲፈቱ በወሰነው መሰረት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑት በይቅርታ አሰጣጥ  መመሪያው ላይ  የተገለፁ፣ የእስራት፣ የዕድሜና የጤና መስፈርቶችን ያሟሉ ናቸው መባሉን ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በመመሪያው ላይ የተከለከሉና በይቅርታ አሰጣጥ መመሪያው ተጠቃሚ የማይሆኑ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 26 የተጠቀሰው ይቅርታን የሚያስከለክሉ ወንጀሎች እንደተጠበቁ ሆኖ በሙስና ወንጀል ተከሰው 10 ዓመት እና ከዛ በላይ የተፈረደባቸው፣ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ላይ የሚፈፀም አስገድዶ መድፈርና ጠለፋ ወንጀል የፈፀሙ ይቅርታው አያካትታቸውም ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተፈረደባቸው፣ የሀሰት ገንዘብ መስራት ወይም ማዘዋወር ወንጀል የተቀጡ ይቅርታው እንደማያካትታቸው ተጠቅሷል፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ያሳዩትን መልካም ስነ-ምግባር ለበደሉት  ህብረተሰብ በልማት ሊክሱት እንደሚገባ ቢሮው አሳስቧል፡፡

ህብረተሰቡም ታራሚዎቹ በፈፀሙት ወንጀል የተፀፀቱ በመሆናቸው ወደ ሕብረተሰቡ ሲቀላቀሉ  አስፈላጊውን ድጋፍ  ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎችም ከጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከያሉበት ማረሚያ ቤት እንዲፈቱ መደረጉም ተገልጿል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.