Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ “የዓለምን ሰላም እያጠፋችው” ነው ስትል ሰሜን ኮሪያ ወቀሰች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ የውክልና ጦርነት በማድረግ የዓለምን ሰላም እያጠፋች ነው ስትል ሰሜን ኮሪያ ወቅሳለች፡፡

በተለይም በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ አሜሪካ የምታደርገው ጣልቃገብነት በመላው አውሮፓ መጠነ ሰፊ ግጭትን ሊያስከትል እንደሚችልም አስጠንቅቃለች።

የኪም ጆንግ ኡን እህትና የሰራተኞች ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን ኪም ዮ ጆንግ ከሀገሪቱ ሚዲያ ኬ ሲ ኤን ኤ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ለዩክሬን የሚያደርጉትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ኮንነዋል፡፡

ዋሺንግተን እና አጋሮቿ የሩሲያን የደህንነት ስጋት ችላ በማለት የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን እያቀረቡ መሆኑን ያነሱት ባለስልጣኗ ይህም የዓለምን ሰላም ስጋት ላይ እንዲወድቅ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

የአሜሪካ ባለስልጣናት የዩክሬንን የከባድ ጦር መሳሪያዎች ድጋፍ ጥያቄ ውድቅ ሲያደርጉ ቢቆዩም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ 31 እና ኤም 1 የተባሉ የጦር ታንኮችን ለዩክሬን ለመስጠት ተስማምተዋል፡፡

ከአሜሪካ በተጨማሪ ጀርመን እና ፖላንድን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት በሚቀጥሉት ወራት ሊዮፓርድ 2 የተባሉ ታንኮችን ለዩክሬን ለመላክ ቃል ስለመግባታቸውም ተሰምቷል፡፡

ሞስኮ ይህን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ስትቃዎም የቆየች ሲሆን የጦር መሳሪያ ድጋፉ ግጭቱን ለማራዘም እና ከኔቶ አባል ሀገራት ጋር ቀጥተኛ ግጭት ለመፍጠር የሚደረግ ነው በማለት ስትኮንን ቆይታለች፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ  ይህ ዓይነቱ  ወታደራዊ ዕርዳታ ሩሲያን ከአላማዋ እንደማያግዳት ሲናገሩ ቆይተዋል።

ቃል አቀባዩ የምዕራባውያን ታንኮች በዩክሬን ጦር ሜዳ ላይ ይወድማሉ ማለታቸውን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.