Fana: At a Speed of Life!

ማህበሩ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር የ212 ሚሊየን ብር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እና ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የ2023 የሁለትዮሽ ትብብር ስምምነት ተፈራረመዋል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ፀሃፊ አቶ ጌታቸው ታዓ እና የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ልዑክ ኃላፊ ኒኮላስ ቮን አርክስ ተፈርራመውታል፡፡

የትብብር ስምምነቱ ለግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በተለይም በትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል-ጉሙዝ የሰብዓዊ ድጋፎችን በተደራጀ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።

በስምምነቱ መሰረትም በፈረንጆቹ በ2023 በጀት ዓመት 212 ሚሊየን 493 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ እንዲሁም 44 ሚሊየን ብር በዓይነት ለማህበሩ ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

አቶ ጌታቸው ታዓ÷ ትብብሩ የማህበሩን ሁለንተናዊ አቅምን ለመገንባት፣ የልማት ስራዎችን ለማገዝ እና በግጭት የተጎዱ ሰዎችን ለማቋቋም የተጀመረውን ስራ በሚፈለገው ደረጃ ማሳለጥ ያስችላል ብለዋል፡፡

ማህበሩ በመላ ሀገሪቱ በጦርነትና በተፈጥሮ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እና ግጭቶችን ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ልዑክ ኃላፊ ኒኮላስ ቮን አርክስ በበኩላቸው÷ ስምምነቱ በአደጋ ጊዜ የሰብዓዊ ድጋፎችን ምላሽ ለመስጠት የማይተካ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

በስምምነቱ መሰረት በጦርነት፣ በድርቅና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ተባብረው እንደሚሠሩም ኃላፊው መናገራቸውን ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.