አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ከሶማሌ ክልል ተወላጅ ዳያስፖራዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ በልማት ስራ ለመሳተፍ ከመጡ የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ ሙስጠፌ በራሳቸው ተነሳሽነት በሀገር ወዳድ ስሜት በክልሉ ልማት ላይ ለመሳተፍ ወደ ክልሉ ለመጡት የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
መንግስት ወደ ክልላቸውና ህዝባቸው ለሚመለሱ የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በውይይቱ ዳያስፖራዎች በአፍዴር ዞን ሀርገሌ ከተማ ለሚገኙ ወላጅ አልባና የኑሮ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ወገኖች በሚገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡