Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች የተካሔደው ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ተጠናቆ ቆጠራ ተጀምሯል – ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሄደው የሕዝበ ውሣኔ ድምፅ አሰጣጥ ሒደት ተጠናቆ ቆጠራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
 
ቦርዱ በክልሉ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ ዞኖች እና ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ላይ ዛሬ የተካሄደውን የሕዝበ ውሣኔ ድምፅ መስጠት ሂደትን በተመለከተ ዛሬ ማምሻውን መግለጫ ሰጥቷል።
 
የድምጽ አሰጣጥ መርሐ ግብሩ ዛሬ ከማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት በ31 ማዕከላት ሥር በሚገኙ 3 ሺህ 771 ምርጫ ጣቢያዎች መከናወኑን የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ገልፀዋል።
 
በአብዛኛው ምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጠቱ ሂደት 12 ሰዓት ላይ ተጠናቆ ምርጫ ጣቢያዎች እንዲዘጉ መደረጉንም ነው የተናገሩት።
 
በክልሉ 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች የተካሄደው ህዝብ ውሳኔ ምርጫ ጥቂት የአሰራር ክፍተቶች ከማጋጠሙ በቀር ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከናወኑንና መራጩ ሕዝብም ችግር ሳያጋጥመው ድምፁን ሲሰጥ መዋሉን ገልጽዋል።
 
በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ ቆጠራ መጀመሩን የጠቅሱት ሰብሳቢዋ÷በድምፅ አሰጣጥ ሂደት ካጋጠሙ የአሰራር ግድፈቶች መካከልም ለአካለ መጠን ያልደረሱ 18 ዓመት ያልሞላቸው ዜጎች በመራጭነት ተመዝግበው መገኘታቸው ጠቁመዋል፡፡
 
በአስተዳደር አካላት በበሌ ማዕከል በሶርቶ ምርጫ ጣቢያ የመታወቂያ ወረቀት የማደል የተፈፀመ የህግ ጥሰቶችን ማንሳታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ህዝብ ውሳኔው ሰላማዊ በሚባል መልኩ የተካሄደ መሆኑን ጠቁመው÷ ሆኖም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በነበረበት የፖሊስ ሃይል እጥረት የተነሳ ሚሊሻዎች በተወሰኑ ጣቢያዎች ላይ መመደቡን ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።
 
የእነዚህና የሌሎችም ግድፈቶችና የህግ ጥሰቶች መረጃ የተሰበሰበው ከቦርዱ የጥሪ ማዕከል፣ ታዛቢዎችና በቦርዱ አመራር አባላት በተደረገ ክትትል መሆኑንም አብራርተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.