Fana: At a Speed of Life!

አምራች ኢንዱስትሪውን በፋይናንስ በመደገፍ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል- አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአምራች ኢንዱስትሪው የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የፋይናንስ ተቋማት አምራች ኢንዱስትሪውን በፋይናንስ እንዲደግፉ ያለመ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት አምራች ኢንዱስትሪውን በማበረታታት ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በ10 ዓመቱ ለ10 ሚሊየን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል ተብሏል፡፡

ዘጠኝ ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱም ነው የተገለጸው፡፡

ዕቅዱ እንዲሳካም በፋይናንስ መታገዝ እንዳለበት ነው አቶ መላኩ በአጽንኦት የገለጹት፡፡

አምራች ኢንዱስትሪው እያገኘ ያለው የፋይናንስ ድጋፍ 19 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቁመው÷ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶው ከልማት ባንክ የሚገኝ ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡

የንግድ ባንኮች ሚና አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የፋይናንስ ተቋማት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ብድር ከመስጠት ጀምሮ ቀልጣፋ አሠራርን በመዘርጋት ዘርፉን ማበረታታት እንደሚገባቸው ነው የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም ቁጠባን በማበረታታት አምራች ኢንዱስትሪዎች በቀላሉ ገንዘብ የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠርና ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ ይገባል ተብሏል።

በአፍሪካ ኢንፖርት ኤክስፖርት ባንክ የኢስት አፍሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ  ኩዳኩሼ ማተሬኬ÷ ከኢትዮጵያ መንግስትና የንግድ ባንኮች ጋር አብረው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከንግድ ባንኮች ጋር በመሆን አምራች ኢንዱስትሪውን የሚደግፍ ስራ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.