Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሱዳን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የሱዳን መንግስታት በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂና ቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች በትብብር መስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ እና የሱዳን ሪፐብሊክ የቴሌኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር አደል ሐሰን መሐመድ ተፈራርመውታል፡፡

ዶክተር በለጠ ሞላ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ እና ሱዳን እህትማማችና የረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ድንበር የሚጋሩና የአንድ ወንዝ ልጆች መሆናቸውን ጠቅሰው ÷ በሳይንስ ቴክኖሎጂና በኮሙኒኬሽን ዘርፍ ተባብረው ለመስራት መነሳሳታቸው ተገቢና ወቅታዊ ነው ብለዋል፡፡

ሀገራቱን ዘመኑ በሚጠይቀው የቴሌኮሙኒኬሽን፣ ኢንፎርሜሽንና ዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የህዝቦቹን ኑሮ ማሻሻል ከመንግስታት እና ከዚህ ትውልድ ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡

ስምምነቱን ወደ ተግባር የሚቀይሩና በዘርፉ ውጤት የሚያመጡ እቅዶች ተነድፈው እንዲተገበሩ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡

አደል ሐሰን መሐመድ በበኩላቸው÷ ልዑኩ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በቴሌኮምና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ለመስራትና ዲጂታል ኢኮኖሚን በጋራ ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ለመፈራረም መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ ስምምነቱን ለመተግበር እንደሚሰራም መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።

በቀጣይ የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተልና የሚያስፈጽም የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ በጋራ ተቋቁሞ ወደ ስራ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.