Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የአንድ ጤና መርሐ ግብርን ለመተግበር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የአንድ ጤና (ዋን ሄልዝ) መርሐ ግብርን ተግባራዊ ለማድረግ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቴክኒካል ኦፊሰር ዶክተር ሞሃመድ ኢብራሂም÷ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም በኢትዮጵያ የአንድ ጤና (ዋን ሄልዝ) መርሐ ግብርን ተግባራዊ ለማድረግ ከተቋቋመው ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ከሆኑት ጤና ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙንም አንስተዋል፡፡

በዚህ መሰረት ድርጅቱ ለመርሐ ግብሩ ትግበራ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው ዶክተር ሞሃመድ የተናገሩት፡፡

አሁን ላይም በኢትዮጵያ ያለውን የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ማሻሻል ለሚያስችለው የአንድ ጤና መርሐ ግብር የአቅም ግንባታ፣ የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የዓለም ጤና ድርጅት መርሐ ግብሩን ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ስጋት የሆኑ በሽታዎችን በዘላቂነት ለመከላከልም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጤና ስርዓቱ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.