Fana: At a Speed of Life!

በባሕርዳር ከተማ፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር፣ የጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየሠሩ መሆኑን ገለጹ።

የስራ ኃላፊዎቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት ወደ አካባቢዎቹ የሚመጣ ጎብኚ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡

የባሕርዳር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ጋሻው እንዳለው እንደገለጹት፥ ቀደም ሲል የመሠረተ ልማት ሥራ የተከናወነላቸው መስኅቦች ለጎብኚዎች ምቹ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

ሌሎች መስኅቦችንም በቀላሉ ለጎብኚ ተደራሽ ለማድረግ ወደ ጭስ ዓባይ ፏፏቴ እና ዘጌ የሚወስዱ መንገዶችን ጨምሮ በተለያዩ መዳረሻዎች ላይ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው ብለዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ኦባንግ ኦቻላ በክልሉ የሚገኙ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ መስኅቦች ፕሮፋይል መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

አንዳንዶቹ መስኅቦች ለጎብኚ እንዲመቹ ሆነው እየለሙ መሆናቸውን እና ቀሪዎቹን ለማልማትም የክልሉ መንግሥት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር ሽመልስ እንድሬ የቢጀሚዝ ብሄራዊ ፓርክ በክልሉ ምክር ቤት እውቅና ማግኘቱን እና የማኦ-ኮሞ እንዲሁም የካማሽ እጩ ብሄራዊ ፓርኮች በጥናት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የመሐመድ ባንጃው ቤተ መንግስት ይዘቱን ጠብቆ እንዲጠገን ከቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የመስኅብ ሥፍራዎችን በመንገድ መሠረተ ልማት በማስተሳሰርና በቀላሉ ለጎብኚዎች ተደራሽ በማድረግ ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየሠሩ መሆናቸውንም ነው የሥራኃላፊዎቹ የተናገሩት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.