Fana: At a Speed of Life!

ለበዓላቱ ከግማሽ ሚሊየን ኩንታል በላይ ስኳር ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለቀጣዮቹ የትንሳኤ እና ዒድ ዓልፈጥር በዓላት ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
 
በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድና ሸማቾች ጥበቃ መሪ ስራ አስፈጻሚ መስከረም ባህሩ እንደገለጹት÷ ለበዓላቱ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
 
በተለይም በበዓላት ወቅት ይበልጥ ተፈላጊ ለሆኑ እና እጥረት በሚከሰትባቸው ምርቶች ላይ በየደረጃው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
 
ከስኳር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ባለፉት ወራት በሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች የምርት እጥረት በመኖሩ ሳቢያ ክልሎች ከነበራቸው ኮታ ሩብ ያህሉን ብቻ ሲወስዱ እንደነበር አንስተዋል፡፡
 
አሁን ላይ በስኳር ኮርፖሬሽን ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ የስኳር ክምችት መኖሩን ጠቁመው÷ ለበዓላቱ ክልሎች ከሚወስዱት ኮታ 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ያህሉን እንዲወስዱ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
ለበዓላቱ የሚያስፈልጉ የግብርና እና ሌሎች ምርቶችን በስፋት ለማቅረብም ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
ምርቶቹ በቅዳሜ እና እሑድ ገበያዎች ላይ በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡ አቅጣጫ መቀመጡምን ስራ አስፈጻሚዋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
 
በበዓላት ወቅት ህገ ወጥ ነጋዴዎች በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉም ቁጥጥር እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.