Fana: At a Speed of Life!

በሀረሪ ክልል “የመደመር ትውልድ” መፅሐፍ የማስተዋወቂያ መርሃግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በሀረሪ ክልል”የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ የማስተዋወቂያና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር በክልል ደረጃ በሐረር ከተማ ተካሄደ።

ከመፅሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በሀረር ከተማ የቱሪስት መስህብ የሆነውን የጅብ ማብያ ስፍራን ለማስዋብና ለጎብኚዋች ምቹ ለማድረግ የጅብ ማብያ ፓርክ ለመገንባት ተወስኗል።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት÷ የመደመር ትውልድ ሰላምን ፣መቻቻልን፣ መተጋገዝን፣አብሮነትን፣ አስተውሎትንና መተማመንን የሚገነባ ማህበራዊ መሠረትን መገንባት፣ ልህቀትን መሻት መገለጫዎቹ ናቸው።

ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የጅብ ማብያ ፓርክ ሲገነባ የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ የወጣቶች ስራ አጥነትን ለመቀነስ፣ የውጭ ምናዛሪ ለማግኘትና ገቢን ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጉ በተጨማሪ እርስ በርስ ለመተዋወቅና ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር አስተዋፅኦ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ሁሉም የክልሉ ነዋሪና ባለሃብቶች መጽሐፉን በመግዛት በትውልድ ግንባታ ሂደትና ሀረርን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ከ “የመደመር ትውልድ” ማስተዋወቂያ እና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ከ80 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡
በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.