የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 6፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፥ “የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ለሁለት ቀን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደኅና መጡ” ሲሉ ገልጸዋል።
ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር አጋዥ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱት።
ጆርጂያ ሜሎኒ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ ከመንግስትና ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጠቅላይ ሚኒስትሯ ጉብኝት ጣልያን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሰብዓዊና የልማት ድጋፍ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምክር እንደሚሆንም ተጠቁሟል።
ጉብኝቱ የኢትዮጵያ እና የጣልያንን አጋርነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ኢትዮጵያና ጣሊያን በሚጋሯቸው ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉም ተጠቅሷል።