Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንደምትደግፍ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና÷ በኢትዮጵያ መንግስት የሚከናወኑ የመልሶ ግንባታ እና የማገገሚያ ሥራዎችን እንደምትደግፍ አስታወቀች፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሠጡት መግለጫ÷ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ግጭት አክትሞ የተለያዩ የሠላም ሒደቶች መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡

ይህም በፍላጎቶች መካከል ያለውን ቅራኔ ለማስታረቅ እና በንግግር አንድነትን ለማረጋገጥ አበረታች እመርታ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ከሠላም ሒደቱ የተገኘው ውጤት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍላጎት እና ድል ነው ያሉት ማኦ ኒንግ÷ በቻይና መንግስት ስም ለኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ዘላቂ ሠላምና ደኅንነት ትልቅ ፋይዳ አለው ማለታቸውንም ሺንዋ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅ የምትወስዳቸውን የተለያዩ አማራጮች ቻይና በጽኑ እንደምትደግፍም ማኦ ኒንግ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የሚደረጉ ንግግሮችን ቻይና በመልካም ጎን እንደምትመለከታቸውና መግባባት ላይ ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶችን ስትደግፍ መቆየቷን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውስጥ ግጭት እንዲያከትም እና ሠላም እንዲሰፍን አስተዋፅዖ ላበረከቱ አካላት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዕውቅና መሥጠታቸው ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.