በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ አምስት ግለሰቦች ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በወሰደው ህግ ማስከበር ስራ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ አምስት ግለሰቦች ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ተፈቀደ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት መንግስት በወሰደው ህግ ማስከበር ስራ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ አምስት ግለሰቦችን የጥርጣሬ የመነሻ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብን ተመልክቶ ነው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ የፈቀደው።
ተጠርጣሪዎቹ መንበረ አለሙ ተከታይ፣ ሲሳይ መልካሙ አበበ፣ ገብረዓብ አለሙ ዘሪሁን (ዶ/ር)፣ ተስፋዬ መኩሪያው አበባው እና ወንዶሰን ተገኝ ተስፋዬ ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ መርማሪ ትናንት ከሰዓት በኋላ በነበረ ቀጠሮ ለችሎቱ ቀርቦ እንዳብራራው÷ ተጠርጣሪዎቹ በአመራሮች ላይ ጥቃት ለመፈፀም እና ግድያን ለማስቀጠል ፣ ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በማሰብ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስረድቷል።
በተለይም 1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪዎች በአማራ ክልል አመፅና ብጥብጥ እንዲነሳ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለወንጀል ተግባር የሚሳተፉ ተማሪዎችን ሲያደራጁ እና ሲያሰለጥኑ ነበር በማለት መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።
በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ሲንቀሳቀሱ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር ስራ አራቱ ግለሰቦች በአማራ ክልል አንዱ ተጠርጣሪ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል።
የተጀመረውን የምርመራ ስራን አጠናክሮ ተጨማሪ ማስረጃ አካቶ ለመቅረብም የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፖሊስ ጠይቆ ነበር።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው በፖሊስ በተገለፀው የሽብር ተግባር ውስጥ ተሳትፎ የለንም ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን የዋስ መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
የተጠርጣሪዎችን የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በይደር የተመለከተው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱም ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ያስፈልገዋል በማለት የ14 ቀን ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ