Fana: At a Speed of Life!

ከዓየር ትራንስፖርት ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ይበልጥ ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከዓየር ትራንስፖርት ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር 11ኛውን የአየር ትራንስፖርት ባለድርሻ አካላት የሁለት ቀናት ውይይት በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ሥሜ (ዶ/ር ) ÷ የዓየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት የዓየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰውበበኩላቸው ÷ የዓየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴውን የተሳለጠ በማድረግ የአፍሪካዊያንን ግንኙነት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዓየር መንገድም በፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤ በመቃኘት ለአኅጉሪቷ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ መነቃቃት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በቀጣይም የበረራ መዳረሻውን በማስፋት ለአፍሪካዊያን የበለጠ አገልግሎት ለመሥጠት በትብብር መስራት እንደሚቀጥል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አብዱራህማን በርቴ በበኩላቸው ÷ማኅበሩ የአፍሪካውያንን የዓየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ምቹ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.