Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን ቢዝነስ ፎረም ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ከፓኪስታን መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።

በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ÷ ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ለቢዝነስ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር ከፓሊሲ ጀምሮ የአስራር ማሻሻያዎችን እንዳደረገች ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሃይል አቅርቦት፣  መሰረተ ልማት አውታሮች ግምባታ እና በሰው ሃይል ልማት አንፃራዊ  አቅም እንዳላት ያስረዱት ሚኒስትር ዴዔታው፥ የፓኪስታን ባለሃብቶች እነዚህን እድሎች በመጠቀም ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣይነት ባለው ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ላይ እንደምትገኝ ጨምረው የተናገሩት  አምባሳደር ምስጋኑ መንግስት እድገቱን ጠብቆ ለማስቀል በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የፓኪስታን ንግድ እና ልማት ባለስልጣን ሚኒስትር ዴኤታ ዙቤር ሞቲዋታ ደግሞ በበኩላቸው÷  አፍሪካ መጪዋ የአለም እድገት ማዕከል እንደመሆኗ ከኢትዮጵያ የምናጠናክረው የንግድ ግንኙነት የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራት የንግድ ልውውጥ መጠን እንዲያድግ ብቻ ሳይሆን ሚዛኑ የጠበቀ እንዲሆን እንደምትፈልግም ገልፀዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ሀገራቸው በኢንዱስትሪው ዘርፍ የፈጠረችውን አቅም በመጠቀም ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ንግድ እና ኢንቨስትመንት የማሳደግ ስራ እንደሚሰራ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በፎረሙ ላይ የሁለቱ ሀገራት ንግድ ምክር ቤቶች አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.