የኢንዱስትሪ ልማት ኢኮኖሚውን እንዲያሳድግ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተመለከተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ልማት በኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሰረት የሚጥል መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ታምርት አገራዊ ንቅናቄ የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የንግድ ኤክስፖ ተካሄደ።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ በኤክስፖው ላይ የቀረቡ ምርቶችን ጎብኝተዋል።
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ ኤክስፖው ኢትዮጵያ በዘርፉ ትልቅ አቅም ያላት መሆኑን ያየንበት ነው ያሉ ሲሆን ሌሎች ባለኃብቶችንም ወደ ዘርፉ ለመሳብ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ለአንድ ዓመት የዘለቀው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ትልቅ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ልማት በኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሰረት የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጀመሩ ትልልቅ ግቦችን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ድጋፍን ማጠናከር ይገባልም ነው ያሉት፡፡