Fana: At a Speed of Life!

ከጤፍ ዱቄት ጋር ሰጋቱራ በመቀላቀል ለሕብረተሰቡ ሊያከፋፍሉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጤፍ ዱቄት ጋር የተለያዩ ባዕድ ነገሮችንና የእንጨት ፍቅፋቂ (ሰጋቱራ) በመቀላቀል ለሕብረተሰቡ ሊያከፋፍሉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ሕገ-ወጥ ተግባሩ ሲፈፀም የነበረው በመዲናዋ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ ቆሼ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ መጋዘን ውስጥ ነው፡፡

በመጋዘኑ ውስጥ 47 ኩንታል ምንነታቸው ያልታወቀ ስራ ስርና የእንጨት ፍቅፋቂ (ሰጋ ቱራ)፣ 167 ኩንታል የጤፍ ዱቄት ተከማችቶ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

ባዕድ ነገሩን ከዱቄቱ ጋር የሚደባልቅ መጋዘኑ ውስጥ እንዳይወጣ የተቆለፈበት ሠራተኛ በፍተሻ መገኘቱንም ነው ፖሊስ ያስታወቀው።

የጅማ በር አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከአካባቢው ማህበረሰብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በስራ ላይ የነበረውን ተጠርጣሪ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

በተደረገው ተጨማሪ ምርመራም የንብረቱን ባለቤት አፈላልጎ በመያዝ ተገቢው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሕብረተሰቡ ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ሲመለከት ለፖሊስ አጋልጦ በመስጠት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጠይቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.