Fana: At a Speed of Life!

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የተወሰኑ የዲሲፕሊን ቅጣቶች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 23ኛ ሳምንት በአዳማና በሃዋሳ ከተማ በተደረጉ ጨዋታዎች አምስት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 17 ጎሎች ተቆጥረዋል።

በሳምንቱ 46 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ፤ አምስት ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች ቀይ ካርድ ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ እሁድ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

በተጫዋችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች 7 ተጫዋቾች ላይ ቅጣት የተላለፈ ሲሆን÷ ሱራፌል አወል ከለገጣፎ ለገዳዲ፣ ደጉ ደበበ ከወላይታ ድቻ እና ሙሉቀን አዲሱ ከሲዳማ ቡና ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀማቸው በቀይ ካርድ ከሜዳ በመወገዳቸው በፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱ ተወስኖባቸዋል፡፡

አበበ ጥላሁን ከአርባምንጭ ከተማ እና ማታይ ሉል ከኢትዮ ኤሌትሪክ በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1 ሺህ 500 ብር እንዲከፍሉ ውሳኔ መታላለፉ ተገልጿል፡፡

አለልኝ አዘነ ከባህር ዳር ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ ሃይማኖታዊ መልዕክት የሚያስተላልፍ ምስል በውስጥ ልብሱ ደርቦ መልበሱ ሪፖርት ስለተደረገበት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት የገንዘብ ቅጣት ብር 3 ሺህ ብር እንዲሁም ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 10 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡

ውሀብ አዳምስ ከወልቂጤ ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ ወቅት ከዳኛ እይታ ውጭ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን በክርን ስለ መምታቱ ሪፖርት የተደረበት ተጫዋቹ በፈጸመው ጥፋት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት አራት ጨዋታ እንዲታገድና ብር 3 ሺህ እንዲከፍል ተወስኗል።

በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶችም የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል።

ለገጣፎ ለገዳዲ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ከአራት በላይ ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 5 ሺህ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡

ወላይታ ድቻ በ22ኛ ሳምንት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት በመቅረቡ የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ 50 ሺህ ብር እንዲከፍል መወሰኑ ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ተጫዋቾች የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታድየም መልበሻ ክፍል ሁለት በሮች ስለመስበራቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን÷ ክለቡ የተሰበሩትን በሮች እንዲያሰሩ ወይም የዩኒቨርስቲው አስተዳደር የሚያቀርበውን የንብረት ዋጋ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡

በተጨማሪም በፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ የ23ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ መድን ና ሲዳማ ቡና ግጥሚያ ዙሪያ ምርመራ እያደረገበት በመሆኑ የኮሚቴው የቅድመ ምርመራ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ የጨዋታው ውጤት እንዳይጸድቅ እና ከጨዋታው ጋር የተያያዙ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እንዲታዩ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ወስኗል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.