Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ ለእጀባ፣ ለበረራ ደኅንነት መኮንኖችና አመራሮች ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን አስመረቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሀገር መሪዎችን፣ ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ከአደጋ የመጠበቅና የበረራ ደኅንነነትን የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት ለመፈጸም የሰው ኃይሉን በተከታታይ ስልጠናዎች እያበቃ መሆኑን ገለጸ።
 
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለሪፐብሊካን ጋርድና ለአገልግሎት መስሪያ ቤቱ እጀባ ፣ለበረራ ደኅንነት መኮንኖችና አመራሮች ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና ያጠናቀቁ ሰልጣኞችን አስመርቋል።
 
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው፥ በትብብርና በአጋርነት አብረውት ከሚሰሩ የውጭ መረጃና ደኅንነት ተቋማት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ስልጠና በዋናነት በቪ አይ ፒ ደኅንነት ጥበቃ፣ በፈንጂ ምህንድስና ፣ በድሮን አጠቃቀም ቅየሳና የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
 
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ አደጋ መቼና እንዴት እንደሚከሰት በእርገጠኝነት መናገር ባይቻልም በማያቋርጥ ስልጠናና ልምምድ ብቁና ሁልጊዜም ዝግጁ ሆኖ መገኘት አስፈላጊ በመሆኑ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ይህ አይነቱን ስልጠና አዘጋጅቷል።
 
በመሆኑም አገልግሎት መስሪያ ቤቱ የሀገር መሪዎችን ፣ቁልፍ መሰረተ ልማቶችን ከአደጋ የመጠበቅ እንዲሁም የበረራ ደኅንነትን የማረጋገጥ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም የሰው ኃይሉን በተከታታይ ስልጠና እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
 
ሰልጣኞችም በስልጠና ወቅት በንድፈ ሃሳብ፡ በተግባርና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስልጠና ማግኘታቸው ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬታማ አፈፃፀም ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት።
 
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው የቪ አይ ፒ ደኅንነት ጥበቃ መኮንኖች ከፍተኛ ደኅንነታዊ አንድምታ ያላቸውን ግለሰቦች ደኅንነት ለመጠበቅ ተገቢውን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ አስተሳሰብ እና ስነምግባር ሊጨብጡ ይገባል ብለዋል።
 
እያንዳንዱ የቪ አይ ፒ ደኅንነት ጥበቃ ስምሪት ሊያጋጥሙ ከሚችሉ እንዲሁም ከሚገመቱና ካልተጠበቁ ስጋቶች እና ጥቃቶች የሀገር መሪዎችን፣ ቁልፍ የመሰረት ልማት ተቋማትን በብቃት ለመከላከል የሚያስችል የተሟላ ዕቅድ አዘጋጅቶ የመሰማራት ባህልን ማዳበር እንደሚገባም ገልፀዋል።
 
በብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በንደፈ-ሃሳብና በተግባር የተሰጠውን ስልጠና የተከታተሉ ሰልጣኞችም በስልጠና ያገኟቸውን ዕውቀትና ክህሎቶች በተግባር ልምምድ ማሳየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመላክቷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.