Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ በሰጠው ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አመራር የሀገረ መንግስት ግንባታን የሚያፋጥኑ ስራዎች ተከናውነዋል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ በሰጠው ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አመራር የሀገረ መንግስት ግንባታን የሚያፋጥኑ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ቆይታ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በገለፃቸውም÷የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ በሚቻልባቸው በተለያዩ ነጥቦች ላይ ኮሚቴው መወያየቱን አንስተዋል፡፡

በተለይም በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ አቅሞችን ማዳበር በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ብልፅግና ፓርቲ በተከተላቸው ጠንካራ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ምክንያት በተለያዩ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውና ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ግንባታን የሚያፋጥኑ ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተው ይበል የሚያሰኝ ውጤት እንደተመዘገበ ተናግረዋል።

እንደ ሀገር የትስስር ትርክትን በማጎልበት የህዝቦችን አንድነት እና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርም ብልፅግና ፓርቲ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ይህም ፍላጎት በመሰረታዊነት መሬት ወርዶ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንዲረዳ የተቋቋመውን አካታች ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መርህን በጠበቀ አኳኃን መንግስት በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በፖለቲካው ዘርፍ የተሰሩ ሰፋፊ እና ውጤታማ ስራዎች መኖራቸውን በበጎ መመለከቱን ያነሱት አቶ አደም÷ በተለይም የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የማስፋት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የትብብርና የፉክክር ሚዛኑን ጠብቆ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ተቀራርቦ የመስራት እና ነፃ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሥራ በጥንካሬ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መገምገሙን ጠቅሰዋል።

ዘላቂና አዎንታዊ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያም ዘመናዊ እና ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን አጣምሮ በመጠቀም እና አዎንታዊ ሰላም ለማረጋገጥ የሚረዱ ሥራዎች በትኩረት መሰረታቸውና ውጤትም እየተገኘባቸው መሆኑን የብልጽግና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መገምገሙን አቶ አደም አንሰተዋል፡፡

ሰላምን በማረጋገጥና ዋናው ግባችን የሆነውን ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዞ ይበልጥ ለማፋጠን እንዲቻል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተደረገው ጥረት እጅግ አበረታች ውጤት እንዳስመዘገበ አውስተዋል፡፡

በቀጣይም የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ሃይሎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መርህን መሰረት ባደረገ አኳኃን መቀጠል እንዳለባቸው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልፀዋል።

የህግ የበላይነትን የማስከበር፣ ነፃነትን አጠቃቀምን በአግባቡ ማስተዳደደር፣ የመንግስትን ሃይልን በብቸኝነት የመጠቀም ስልጣንን ማስከበርና የነጠላ ቡድናዊ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈፀም ጥረት የሚያደርጉ አካላትን መታገል በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሁሉም ሕዝቦች የወል እውነቶች ገዢ ሐሳቦች የሆኑባት እንድትሆንና ሀገራዊ አንድነት በጽኑ ሕብረብሔራዊነት የመገንባት ስራን አጠናክሮ መቀጠል እና የፍትህ እና የፀጥታ ተቋማት አቅምን ይበልጥ ማዳበር በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውም ተመላክቷል።

ሌላው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የተወያየበት ነጥብ ሀገራዊ የኢኮኖሚ አቅሞችን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ነው ብለዋል።

ባለፉት 10 ወራት አካታች የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን ለመገንባት በተደረጉ ጥረቶች አበረታች ውጤቶች መኖራቸውና በግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የቱሪዝም መስህቦችን የማልማት ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ይህንንም ማስፋት እንደሚገባ ኮሚቴው አፅንኦት ሰጥቶ መወያየቱን ገልፀዋል።

በኢኮኖሚው ዘርፍ ካጋጠሙ ተግዳሮቶች መካከል ዋነኞቹ የዋጋ ንረት፣ የስራ አጥነት ችግር እና ኮንትሮባንድ፣ ህገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴና የመሳሰሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባና እንቅፋቶችን በማስወገድም በየአከባቢው ያሉ እምቅ አቅሞችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የሥራ እድል መፍጠር ብሎም የኑሮ ውድነት በህዝባችን ላይ የሚፈጠረውን ጫና መቀነስ የሚቻልባቸውን እርምጃዎች መውሰድ ላይ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በጥልቅ የተመለከተውና አቅጣጫ ያስቀመጠባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ አደም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በማህበራዊ ዘርፍ የሚታዩ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት አቅጣጫ ላይ ኮሚቴው ትኩረት ሰጥቶ መክሯል።

በትምህርት ዘርፍ ከአፀደ ህፃናት ጀምሮ ችግሮችን ከስር መሰረቱ የሚፈቱ ስራዎችን በመስራት የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ፣ አካዳሚያዊ ነፃነትን የማክበር እና የመጠበቅ እና ከስታንዳርድ በታች የሆኑ የትምህርት ተቋማትን የማሻሻል ስራዎች በጥሩ ሁኔታ መጀመራቸውንና በቀጣይም ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይም የማህበራዊ ዘርፍ አካል በሆነው በጤናው ዘርፍ በሽታን በመከላከል እና አክሞ ከማዳን አኳያ ዘላቂ መፍትሔ በሚሆኑ ጉዳዮች በትኩረት ሲሰራ መቆየቱና ለበለጠ ውጤታማነት ተጨማሪ ጥረቶች ሊኖሩ እንደሚገባ አሳስቧል።

በዲፕሎማሲው ረገድም የተመዘገቡ አበረታች ድሎች መኖራቸውን የቃኘው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስብሰባ የሀገርን እና የህዝብን ክብር የሚያሳድጉ ስራዎች በመስራት፣ለትብብር እና ለጋራ ተጠቃሚነት ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣መርህ ላይ የተመሰረት ግንኙነት በማዳበር እንዲሁም ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሰጠ ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫ በመከተል ተጨባጭ ውጤት መመዝገብ መቻሉንና ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ኮሚቴው አፅንኦት አስቀምጧል።

በአጠቃላይ እስከአሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል፣ ክፍተቶችን ለመሙላት እና ከስርዓት መንፍስት ግንባታና የዜጎችን ህይወት የሚለውጡ ዘላቂነት ያላቸው ሥራዎችን በውጤታማነት ለመስራት የአመራሩ የበለጠ መፍጠንና መፍጠር ወሳኝ መሆኑን የሥራ አሰፈጻሚ ኮሚቴው አጽንኦት ሰጥቶ መወያየቱን አቶ አደም አንስተዋል፡፡

ፓርቲውን የበለጠ ለማጠናከርና ለሕዝብ ቃል የገባውን በብቃት እንዲፈፅም ለማስቻል የውስጠ ፓርቲ አንድነት ማጠናከር፣ ለዚህም የአመለካት ጥራት፣ የአሰላለፍ ግልጽነትና የፓርቲ ተቋማዊ አቅም የበለጠ የሚያሳድጉ የማጥራትና የመገንባት ስራዎችን በቀጣይነት መስራት ወሳኝ መሆኑን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡንም አንስተዋል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ብልጽግና የሀገሪቱን እና ሕዝቦችን ዘላቂ መብትና ጥቅም የበለጠ ለማስከበር በሚያደርገው እንቅሰቀቃሴ ሁሉ ከፓርቲው ጎን ሆኖ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጥሪ ማቅረቡን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.