Fana: At a Speed of Life!

በመስጅዶች እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት ተቀራርቦ መነጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም በፌዴራል እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት አማካኝነት ከተቋቋመ ኮሚቴ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በቅርቡ በአንዳንድ አካባቢዎች መስጅድ ፈርሷል በሚል የተፈጠረውን ችግር ከሚመለከተው አካል ጋር ተቀራርቦ በመነጋገር የጋራ መፍትሄ ለማበጀት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በውይይት መድረኩ ከፌዴራል መጅሊስ ፣ ከአዲስ አበባ መጅሊስ እና ከኦሮሚያ መጅሊስ የተወከሉ የሐይማኖት አባቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተገኝተዋል።

መስጅዶች በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ፈርሰዋል በሚል ምክንያት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሁለት መስጅዶች ላይ በሁለት የጁምዓ ሶላት ቀናት አመፅ ለመቀስቀስ መሞከሩ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

እነዚህ አካላት በቀሰቀሱት ግጭት ምክንያት የንብረትና የአካል ጉዳት እንዲሁም በሰው ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

ይህ አላስፈላጊ ጉዳት መድረሱ በፍፁም አግባብ እንዳልነበረና ከመፈጠሩ በፊት ሊወገድ የሚችል ችግር እንደነበር በውይይቱ መግባባት ላይ መደረሱን የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

አቶ ብናልፍ አንዷለም በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለፁት÷ የሐይማኖት ተቋማት የሰላም ዘብ እንዲሁም ግንባር ቀደም የሰላም ጠበቃዎች ናቸው፡፡

የትኛውንም ችግር መፍታት የሚቻለው በንግግርና በውይይት ብቻ መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የተፈጠሩት ችግሮች ከሃይማኖቱ አባቶች እና ከመንግስት አቅም በታች በመሆናቸው ይህ ኮሚቴ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በቅርበት መነጋገር መጀመሩ አበረታች ነው ብለዋል፡፡

የተጀመረው ውይይት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄም እንደሚያስገኝ እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ኮሚቴው ለዚህ ወቅታዊ ችግር መፍትሄ በጋራ ማፈላለግ ዋነኛ ተልዕኮው ነው ያሉት አቶ ብናልፍ÷ በዚህ አላስፈላጊ ግጭት ምክንያት ላጋጠሙ ጉዳቶችና ጥፋቶች ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የመጅሊስ ተወካይ የኮሚቴው አባላት በበኩላቸው÷ ለሚፈጠሩ ማንኛውም ችግሮች ተቀራርቦ መነጋገርና መወያየት ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያመጣ ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.