Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ብራዚል ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ብራዚል ያላቸውን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማምተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ጊዜው አሁን መሆኑን ጠቅሰው፥ በብራዚል ዳግም ኤምባሲዋን መክፈቷም ግንኙነቱን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ አስታውሰዋል።

ብራዚል በዘላቂ የደን ልማት አስተዳደር፣ በጥጥ ምርትና በአፈር ጥበቃ ላይ ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለችው መልካም አበርክቶም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ አቪዬሽን፣ ቱሪዝም፣ ግብርና፣ ማምረቻው ዘርፍ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በማዕድን እና ኢነርጂ ከብራዚል ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ፍለጎት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የብራዚሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ በበኩላቸው ሀገራቸው በስፖርትና የተለያዩ መስኮች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰው፥ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በሁለቱ ሃገራት መካከል ቀጣይ የፖለቲካ ውይይት እንዲካሄድም መግባባት ላይ መደረሱነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.