Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በግብርና ልማት በቴክኒክ ድጋፎች ከብራዚል ጋር መስራት ትፈልጋለች- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በግብርና ልማት በቴክኒክ ድጋፎች ከብራዚል ጋር መስራት እንደምትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተናገሩ፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ዛሬ ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ካርሎስ ዱአርቴ ጋር በሀገራቱ ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ÷የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ዘርፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ሚኒስትር ዲኤታው አስታውሰው በተለይ ኢትዮጵያ በግብርና ልማት ከብራዚል ጋር በቴክኒክ ድጋፎች መስራት እንደምትፈልግ አስታውቀዋል ።

በስፖርት እና ባህል ዘርፍ ብራዚል ያላትን የዳበረ አቅም ኢትዮጵያ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት በውይይቱ የተገለፀ ሲሆን÷ ይህም ለህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

በተጠቀሱት መስኮች ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ቁልፍ ስራዎች በሁለቱም መንግሰታት ዘንድ በቀጣይነት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራባቸውም አምባሳደር ምስጋኑ አስገንዝበዋል።

የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ካርሎስ ዱአርቴ÷ በኢትዮጵያ እያደረጉ ያለው ጉብኝት የአገራቱን ወቅታዊ የግንኙነት ከፍታ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

በአካባቢ ጥበቃ፣ በአቪዬሽን ፣ በግብርና ፣ስፖርት እና ባህል ዘርፍ ግንኘነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስታቸው እንደሚሰራ ሚኒስትር ዴኤታው ማስታወቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት በመጠቀም የብራዚል ባለሃብቶች በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩም ተጠይቋል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.