Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሳንዶካን ከዓለም የአየር ንብረት ፈንድ እና ከዓለም የአካባቢ ፋሲሊቲ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳንዶካን ደበበ ከዓለም የአካባቢ ፋሲሊቲ እና ከዓለም የአየር ንብረት ፈንድ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፋዊ ስምምነት የቋሚ ኮሚቴዎች ስብሰባ ጎን ለጎን ነው ከሃላፊዎች ጋር የመከሩት፡፡

አቶ ሳንዶካን÷ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥንና የአካባቢ ጉዳይን በሀገሪቱ የረጅም ጊዜ እቅድ በአግባቡ በማካተት በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ የተነሳ ሀገሪቱ ያሰበችው የብልጽግና ትልም እንዳይደናቀፍ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ ተቋማቱ ይህን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

የዓለም የአካባቢ ፋሲሊቲ በአነስተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ ሀገራት ፈንድ እና የአየር ንብረት ልዩ ፈንድ ኃላፊ ቺዙሩ ኦኪ እና የዓለም የአየር ንብረት ፈንድ የአፍሪካ ቀጠና የሀገራት የፕሮግራም ኃላፊ ኤድዋርዶ ዲ ፍሬታስ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በተቋሞቻቸው በኩል ድጋፍ እያገኘች መሆኑን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት ለመስራትና ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ የሚችሉትን ድጋፍ ሁሉ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በየተቋሞቻቸው ያሉ እድሎችን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ ተነሳሽነቶችን ለመለየትና በቴክኒክ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት እቅድ እንዳላቸው መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.