የስድስት ሀገራት አትሌቶችን የሚያሳትፈው የአስመራ ማራቶን የፊታችን እሑድ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ጨምሮ የስድስት ሀገራት አትሌቶችን የሚያሳትፈው የአስመራ ማራቶን በመጪው እሑድ እንደሚካሄድ የኤርትራ ባህልና ስፖርት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኤርትራ ባህልና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዘመዴ ተክሌ ÷በውድድሩ መርሐ ግብር የወንዶች ሙሉ ማራቶን እና የ10 ኪሎ ሜትር የሴቶች ውድድርመዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
በዕለቱ ከማራቶን ውድድር በተጨማሪ የጋራ ማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት እንደሚካሄድም ነው የገለጹት፡፡
በማህበረሰብ አቀፍ ስፖርቱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ተማሪዎች እና የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሏል።
በውድድሩ የኢትዮጵያ፣ኬንያ፣ኡጋንዳ፣ታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን አትሌቶች የሚሣተፉ ሲሆን ÷ተወዳዳሪ አትሌቶች በዛሬው ዕለት አስመራ እንደሚደርሱ ይጠበቃል፡፡
በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ለሚወጡ አትሌቶች ሽልማት መዘጋጀቱን ከኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡