Fana: At a Speed of Life!

አትሌት ለተሠንበት ግደይ በኒውዮርክ ማራቶን እንደምትካፈል ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንጆቹ ሕዳር 5 ቀን 2023 በሚካሄደው የኒውዮርክ ማራቶን ውድድር የሴቶች የ10 ሺህ ሜትር እና የግማሽ ማራቶን የዓለም ሪከርድ ባለቤቷ አትሌት ለተሠንበት ግደይ እንደምትካፈል ተገለጸ።

አትሌት ለተሠንበት ባለፈው ዓመት በቫሌንሲያ በተካሄደው የማራቶን ሩጫ ላይ 2 ሠዓት ከ16 ደቂቃ ከ49 ሠከንድ በመግባት በታሪክ ፈጣኑን ሠዓት ማስመዝገቧ ይታወቃል።

በኒውዮርክ ከተማ በሚካሄደው የማራቶን ውድድር÷ በዓለም ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ ያመጣችው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደምትሠለፍ ተመላክቷል፡፡

አትሌት ያለምዘርፍ የ2022 የለንደን ማራቶን አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል።

የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮና አሸናፊዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጎይቲቶም ገብረሥላሴ በኒውዮርኩ የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲሚየም ደረጃ የጎዳና ላይ ውድድር ትመለሳለች ተብሏል፡፡

ከኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ጋር የቀድሞዋ የኒውዮርክ ማራቶን ሻምፒዮና ሻሮን ሎኬዲ፣ የቦስተን ማራቶን ሻምፒዮናዋ ሄለን ኦቢሪ፣ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ እና የ2021 የኒውዮርክ ማራቶን ሻምፒዮና ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና የማራቶን የዓለም ሪከርድ ባለቤቷ ብሪጊድ ኮስጌይ እንደሚሰለፉም ተነግሯል፡፡

በወንዶች ደግሞ ከኢትዮጵያ የሁለት ጊዜ የዓለም የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ሞስነት ገረመውና የሁለት ጊዜ የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊው አትሌት ሹራ  ቂጣታይሳተፋሉ።

ኔዘርላንዳዊው የኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤት አብዲ ናጌዬ፣ የ2021 የኒውዮርክ ማራቶን ሻምፒዮን ኬኒያዊው አልበርት ኮሪር፣ የሰሜን አሜሪካ የማራቶን ሪከርድ ባለቤቱ ካናዳዊው ካም ሌቪንስ እና በዘንድሮው የኒውዮርክ የግማሽ ማራቶን ውድድር በሦስተኛነት ያጠናቀቀው የሞሮኮው ዙሀየር ታልቢ በውድድሩ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.