Fana: At a Speed of Life!

ዕድሜ ያልገደበው የ101 ዓመቷ አርሶ አደር የስራ ፍቅር

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ101 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ አዛውንት አርሶ አደር እማማ ካሳሳ አገኝ ሾሌ በኮንሶ ዞን ዳኮኬሌ ወረዳ ፋሾ ቀበሌ አርከላ ተብሎ የሚጠራ መንደር የሚኖሩ ብርቱ አርሶ አደር ናቸው፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከእኒህ ብርቱ አዛውንት አርሶ አደር እማማ ካሳሳ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

አዛውንቷ በእርሻና እንስሳት እርባታ ስራ ደፋ ቀና ሲሉ ነበር ያገኘናቸው የስራ ፍቅራቸው ከፊታቸው ይነበባል፡፡

እማማ ካሳሳ ሁለተኛው የፋሺስት ጣሊያን ወረራ በተፈጸመበት በ1928 ዓ.ም ገደማ በእድሜ ታዳጊ እንደነበሩ የታሪክ አጋጣሚዎችን ጠቅሰው ያስታውሳሉ፡፡

እኔ ያኔ ልጅ እያለሁ አባቴ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ጊዜ ዘምቶ በመሰዋቱ ከዛን ጊዜ ጀምሮ የአባታችንን ስራ በመተካት እናታችን ለማገዝ በትጋት መስራት ነበረብን ይላሉ፡፡

ከዛን ጊዜ በኋላም በዚሁ ትጋታቸው በመቀጠል ጠንካራ የልማት አርበኛ ገበሬ እንደወጣቸውና ዛሬም ድረስ በ101 ዓመታቸው እርጅና ሳይበግራቸው በማሳቸው ውለው ሰርተው ይገባሉ፡፡

የልማት አርበኛዋ እማማ ካሳሳ የሚያስቀና የስራ ፍቅርና መውደድ አላቸው።

“ስራ ከፈታሁ ህመም ይሰማኛል፣ ሰውነቴ ስራ ለምዷል፣ እጄ ያለስራ መቀመጥ አይችልም” ሲሉ ይናገራሉ።

“ምንም እንኳን ዘመናዊ ትምህርት ባልማርም በምሰራው የግብርና ስራ ደስተኛ ነኝ “ይላሉ አዛውንቷ፡፡

የእድሜ ባለጸጋዋ እማማ ካሳሳ 10 ልጆች የወለዱ ሲሆን የልጅ ልጆቻቸውን ጨምሮ 54 የቤተሰብ አባላትም አሏቸው፡፡

በአዛውንቷ ታታሪነት ልጆቻቸውም ሆነ የቀየው ነዋሪዎች በመደነቅ አውርተው አይጠግቡም፣ ስራ ፈተው አይተዋቸው እንደማያውቁ ይመሰክራሉ፡፡

እሳቸውም “ሰዎች የኔን ፈለግ ተከትለው በስራ ተግተው ቤተሰቦቻቸውን እንዲያግዙ እመክራለሁ” ይላሉ አዛውንቷ፡፡

ልጆቻቸው የእርሳቸውን አርአያ ተከትለው ተግተው እየሰሩ በመሆኑ በጣም ደስታ እንደሚሰማቸውም እማማ ካሳሳ ነግረውናል፡፡

ታታሪነትን የሚፈልገው የግብርናው ዘርፍ እንደ እማማ ካሳሳ ያሉ ብርቱዎችን ይሻል፣ ግብርና ከስራም በላይ መሆኑን እሳቸው ምስክር ናቸው፡፡

በመለሰ ምትኩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.