Fana: At a Speed of Life!

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሆቴሉን በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች ማረፊያ እንዲሆን ፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሞሮኮ የሚገኘው የግል ሆቴሉ በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች ማረፊያ እንዲሆን ፈቅዷል፡፡

ቶክ ስፖርት እንዳስነበበው÷ በሞሮኮ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው ከተሰማ በኋላ ፖርቹጋላዊው የእግርኳስ ኮከብ በማራካሽ የሚገኘው ሆቴሉ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ክፍት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

“ፔስታና ሲ አር 7” የተሰኘው ይህ የክርስቲያኖ ሮናልዶ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል 174 ክፍሎች ያሉት እና በማራካሽ ውብ ስፋራዎች የተገነባ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ለአንድ ሌሊት ከ130 ፓውንድ በላይ የሚያስከፍለው የሮናልዶ ቅንጡ ሆቴል በአሁኑ ወቅት የአደጋው ተጎጂዎች ጊዜያዊ መጠለያ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በተያያዘ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን  እግር ኳስ ተጫዋቾች በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ  የተጎዱ  ሰዎችን ለመርዳት ደም ለግሰዋል፡፡

በአደጋው ምክንያት ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ  ጨዋታ ከላይቤሪያ  አቻው ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ መሰረዙም ተጠቁሟል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የዌስትሃሙ ተከላካይ  ናዩፍ አጉዌርድ÷ የአደጋውን ዜና ስንሰማ ከላይቤሪያ ጋር የነበረንን ጨዋታ በመሰረዝ ከሕዝባችን  ጎን ለመቆም ወስነናል ብሏል፡፡

በደም ልገሳ መርሐ ግብሩ  የፒኤስጂው ተከላካይ  አሽራፍ ሃኪሚን ጨምሮ በርካታ ስመ ጥር ተጫዋቾች ተሳትፈዋል፡፡

በሞሮኮ ማራካሽ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እስካሁን ከ2 ሺህ 100 በላይ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.