Fana: At a Speed of Life!

ለዓመታት በ16 ኩባንያዎች ተቀጥራ በስራ ገበታዋ ተገኝታ የማታውቀው እንስት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይናዊቷ ጓን ዩ በተመሳሳይ ጊዜ በ16 የተለያዩ ኩባንያዎች መቀጠሯ ከታወቀ በኋላ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰሰች፡፡

ቻይናዊቷ እንስት ጓን ዩ 16 ኩባንያዎች በተለያየ ጊዜ ባወጡት የሥራ ቅጥር በማመልከት አስፈላጊውን መረጃና ሂደት ተከትላለች ይላል ኦዲቲ ሴንትራል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች ያወጡት የሥራ ቅጥር ‘’ታሟላለች’’ በማለትም ‘’ለስራው ብቁ ነሽና በታማኝነት አገልግይን’’ ሲሉ ቅጥር ይፈጽማሉ፡፡

በተለያዬ ጊዜ የተፈጸመው የስራ ቅጥሩ ቢያንስ ለሦስት ዓመታት የዘለቀ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

ይህ ሲሆን አንድም ቀን የትኛውም የሥራ ገበታዋ ላይ ተገኝታ አለማወቋና ደመወዝ ሲከፈላት መቆየቷ አጃዒብ አሰኝቷል፡፡

እሷና በዚህ ክስ የተጠረጠረው ባለቤቷ ስለ ቀጣሪዎች፣ በየኩባንያው ውስጥ ያላትን ትክክለኛ ሚና፣ ለእያንዳንዳቸው መሥራት የጀመረችበትን ቀንና ወርሃዊ ደሞዟን የሚገልጽ የባንክ ሂሳብ ዝርዝር መረጃዎችን በሚስጥር ማስቀመጣቸው ተሰምቷል፡፡

ጓን ዩ ያለማቋረጥ አዳዲስ አሰሪዎችን ትፈልግ እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡

ወደ አዲስ የስራ ቃለ መጠይቆች ስትሄድ፣ ከደንበኞቿ ጋር መገናኘቷን ለማረጋገጥ ፎቶዎችን አንስታ ቀድሞውኑ ወደምትሰራባቸው ቀጣሪዎቿ በመላክ ደንበኞች ጋር እንደሆነች ታስመስላለች ተብሏል፡፡

በዚህ ሁኔታም ለዓመታት ያለምንም እንከን ስታጭበረብር መቆየቷም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህ ሁሉ ኩባንያዎች ውስጥ በምታገኘው ረብጣ ገንዘብም በቻይና ሻንጋይ ውስጥ ውድ ዋጋ ያለው አፓርታማ መግዛቷም ተሰምቷል፡፡

ጓን ዩ የድርጅት ስራን ለማግኘት በምታደርገው የማያቋርጥ ፍለጋ በጣም የተጠመደች ስለነበር ብዙ የስራ ቃለ መጠይቆች በተመሳሳይ ጊዜ ሲከታተሉባት ለሌሎች ሰዎች በማስተላለፍ ኮሚሽን እንደምትቀበልም ነው የተነገረው፡፡

ስኬታማ ሥራ አልሰራሽም ተብላ በተባረረችበት አንዱ ሥራም ምትክ ስራ በማፈላለግ ታካክስ እንደነበርም ተገልጿል፡፡

ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ በአንድ ስሕተት ለዓመታት ያለስራ ሲከፈላት የነበረው ደምወዟን የሚያሳጣ እሷንም ለክስ የሚዳርግ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡

ይሕም ከቀድሞ አሰሪዎቿ አንዷ በኦንላይን ከጓን ዩ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ አገኘች፡፡

የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለቤት የሆኑት ሊዩ ጂያን ዩኢን እና ሌሎች ሠባት ተባባሪዎችን በሽያጭ ቦታዎች ቀጥረው እንደነበርና አንድም ሽያጭ ስላላስገኙ ከሦስት ወራት የሙከራ ጊዜ በኋላ አባረሯቸው።

በዚህ ወቅት ለዚህ ኩባንያ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤዋን ለማስገባት በማሰብ በስሕተት ለሌላ ኩባንያ እና ለብዙ የኦንላይን ስራ እንደላከችና በዚህም የማጭበርበሪያ ስልቷ እንደተነቃባት ተገልጿል።

በዚህም የማጭበርበር ድርጊቷ በቁጥጥር ስር ስትውል ለሌላ የሥራ ቃለ-መጠይቅ ስታደርግ እንደነበርም ነው የተሰማው፡፡

በተጨማሪም ባለቤቷን ጨምሮ ከ50 የሚበልጡ ግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር ውለዋል ነው የተባለው፡፡

የቻይና መገናኛ ብዙሀን እንደዘገበው ይህ ዓይነቱ ማጭበርበር በቻይና የተለመደ ችግር ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.