Fana: At a Speed of Life!

ሜዴሊን – ሙቀትን በአረንጓዴ ልማት ያሸነፈች ኮሎምቢያዊቷ ከተማ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሜዴሊን በኮሎምቢያ የምትገኝ ከቦጎታ በመቀጠል በኮሎምቢያ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ናት፡፡

ከአሥር ዓመታት በፊት የአካባቢው አስተዳደር ለመንገድ ልማት ፕሮጀክት በሚል በመንገድ ላይ ያሉት ዛፎችና ዕፅዋት በሙሉ የተመነጠሩባት ባዶ ሥፍራ ነበረች – ሜዴሊን፡፡

በሜዴሊን “ኦሪየንታል” እየተባለ የሚጠራው ጎዳና ዛሬም እንደቀድሞ ሁሉ በከፍተኛ የትራፊክ ፍሰትና በጥቃቅን የንግድ እንቅስቃሴ የተሞላ ነው።

ነገር ግን ከቀድሞው አረንጓዴ ዕፅዋትን የመመንጠር አስተዳደራዊ ውሳኔ በተቃራኒ አካባቢው ትላልቅ የፍራፍሬ ተክሎችን ጨምሮ በዕጽዋት አረንጓዴ የለበሰና በአበቦች የተዋበ ሆኗል።

አስተዳደራዊ ውሳኔውን ተከትሎ የታየው የጎዳናውን የዓየር ንብረት ለውጥና ቅዝቃዜ ተመስክሮለታል።

አሁን ላይ ኦሪየንታል ጎዳና ዓመቱን በሙሉ መንፈስን የሚያድስ ንጹሕ አየር የታደለና በአረንጓዴ ሽፋን በብዙዎች የሚታይ ውብ ቦታ ሆኗል፡፡

ጎዳናው የብስክሌት መንገዶችንና በጎዳናው ግራና ቀኝ ባሉ አረንጓዴ ዕፅዋት ሥር አረፍ ብለው ንጹሕ ዓየር የሚቀበሉበት አግዳሚ ወንበሮችን ያካተተ ነው፡፡

የሜዴሊን ከተማ ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ ዓመቱን በሙሉ ቱሪስቶችን የሚስብ መሆኑም ተነግሯል፡፡

ሜዴሊን የ”አረንጓዴ ኮሪደሮች” የልማት መርሐ-ግብሯን የጀመረችው በፈረንጆቹ 2016 መሆኑን ቢቢሲ ፊውቸር ፕላኔት ዘግቧል፡፡

በወቅቱ ከ30 በላይ አረንጓዴ ኮሪደሮችን ለማልማት ዕቅድ ነድፋ በተለየ ዕይታ መርሐ-ግብሯን የጀመረችው የአየር ብክለት እና የሙቀት መጨመር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል።

የአረንጓዴ ልማት መርሐ-ግብሩ ÷ የመንገድ ዳርቻዎች፣ የቋሚ ዕፅዋት ሽፋን ፣ ጅረቶችን፣ መናፈሻዎችን እና በአቅራቢያ ያሉ ኮረብታማ ትንንሽ የከተማ ውስጥ መልክዓ-ምድሮችን የሚያገናኝ አስደናቂ ፕሮጀክት ነው፡፡

የመጀመሪያው የፕሮጀክቱ መርሐ-ግብር 120 ሺህ ያኅል ዕፅዋትን እና 12 ሺህ 500 ያኅል ቋሚ ዕፅዋትን በመንገድ እና ፓርኮች አካባቢ በመትከል ተከናውኗል፡፡

በፈረንጆች 2021 ላይ ደግሞ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ያኅል አነስተኛ ዕፅዋትን እና 880 ሺህ ያኅል ዛፎች በመላ ከተማዋ በመትከል የአረንጓዴ ልማት መርሐ-ግብሩ ስኬታማ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡

የከተማን የዓየር ንብረት በመለወጥ እና በማቀዝቀዝ ረገድ አስደናቂ ውጤት ማሳየቱን ተከትሎ ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡

በዓለማየሁ ገረመው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.