የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክለቦች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባው ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የእግር ኳሱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከክለቦች ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አመራሮችና ስራ አስፈፃሚ አባላት ጋር በእግር ኳሱ ዕድገት ተግዳሮቶችና በፌዴሬሽኑ አሰራር ላይ ተወያይቷል፡፡
በዚሁ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ÷ውጤት ለማምጣት ፌዴሬሽኑ በክለቦች ውጤታማነት ላይ አተኩሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ለእግር ኳሱ ውጤት መሻሻል ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መናገራቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷በእግር ኳሱ ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሄ መተግበር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ፌዴሬሽኑ የሀገሪቱን እግር ኳስ ውጤት ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ናቸው፡፡
የበጀት እጥረት፣ የክለቦች ተተኪ ለማፍራት አቅደው አለመስራት፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከውጭ ሀገራት አምጥቶ ለማጫወት ያሉ የሕግ ክፍተቶች፣ ከተለያዩ አካላት ለእግር ኳሱ የሚሰጡ ትኩረቶች ማነስ እና ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም ያለመኖር የኳሱን እድገትና ውጤት እንደጎዳውም ነው የተናገሩት።