Fana: At a Speed of Life!

ተቀዛቅዞ የቆየው የቱሪዝም ዘርፍ እያገገመ መምጣቱ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በመጀመሪያዎቹ ሰባት  ወራት የዓለም ቱሪዝምን በመሳብ 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የዓለም አቀፉ ቱሪዝም ተቋም አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2019 አንጻር 28 በመቶ የቱሪዝም ፍሰት ዕድገት በማስመዝገብ ከዓለም 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ነው ተቋሙ ያስታወቀው፡፡

ቀደም ሲል የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለምአቀፍ ደረጃ መከሰቱን ተከትሎ የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ፍሰት ከፈረንጆቹ ጥር እስከ ሐምሌ ወራት 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በ84 በመቶ የማገገም ሁኔታ አሳይቷል ነው ያለው ተቋሙ፡፡

ዓለምአቀፉ የቱሪዝም ፍሰት በፈረንጆቹ 2023 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በ80 በመቶ ሲያንሰራራ፣ በ2ኛው ሩብ ዓመት ደግሞ በ 85 በመቶ ማደጉን ዓለምአቀፉ የቱሪዝም ድርጅት መረጃ አመላክቷል፡፡

ከፈረንጆቹ ጥር እስከ ሐምሌ 2023 ባሉት ወራት 700 ሚሊየን የሚጠጉ ጎብኚዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ለጉብኝት መንቀሳቀሳቸውንም ነው ድርጅቱ የጠቆመው፡፡

ይህም ከፈረንጆቹ 2022 ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር በ43 በመቶ ገደማ ብልጫ እንዳለው ገልጾ÷ በዓለምአቀፍ ደረጃ ተቀዛቅዞ የቆየው የቱሪዝም ዘርፍ ፍሰት እያገገመ ነው ብሏል፡፡

ከወረርሽኙ ወቅት አንፃር በዚህ ዓመት ሰባት ወራት ውስጥ የአፍሪካ የቱሪዝም ዘርፍ በጎብኝዎች ፍሰት የ92 በመቶ ዕድገት እንዳስመዘገበ የተገለጸ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት የዓለም ቱሪዝምን በመሳብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.