Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ ወጣቶች የእግር ኳስ ጥበብ የሚቀስሙበት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ዋና ፀሐፊ ማዳም ፋጡማ ሳሞራ ወጣቶች የእግር ኳስ ጥበብን በትምህርት ቤቶች የሚቀስሙበትን “እግር ኳስ -ለትምህርት ቤቶች” ፕሮጀክት በድሬዳዋ ይፋ አደረጉ።

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ዘርፍ ያላትን ደረጃ ለማሳደግና ተተኪ ወጣቶች በእግር ኳስ ጥበብ መሠረታዊ ዕውቀት እንዲጨብጡ ያግዛል ተብሏል።

በዋና ፀሃፊዋ የተመራ የፊፋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና አሰልጣኞች ልዑክ በድሬዳዋ እየተሰሩ ያሉ የእግር ኳስ መሠረተ ልማት ግንባታዎችንም ተመልክቷል።

በጉብኝቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና የካቢኔ አባላት እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚደንት ኢሳያስ ጅራ ተሳትፈዋል።

ልዑኩ በ50 ሚሊየን ብር ወጪ በድሬዳዋ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ የተነጠፈውን ሰው ሰራሽ የሣር ሜዳ እንዲሁም ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውን ሁሉን አቀፍ የስፖርት አካዳሚ ተመልክተዋል።

በዚሁ ጊዜ የፊፋ ዋና ፀሐፊ ፋጡማ እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያ በዓለም የእግር ኳስ ዘርፍ የሚገባትን ስፍራ እንድታገኝ እየተገነቡ ያሉ የስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አጋዥ ናቸው፡፡

እነዚህን ልማቶች በሚፈለገው ጥራት ተገንብተው ውጤት እንዲያመጡ ፊፋ የሚያደርገውን ሙያዊና ቴክኒካል ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የካፍ መስራችና ታላቅ ሀገር መሆኗን ገልጸውም ÷ በድሬዳዋና በመላው ሀገሪቱ እየተገነቡ የሚገኙ የእግር ኳስ መሠረተ ልማቶችን በማጠናከር በ2026 አፍሪካን በዓለም ዋንጫ ከሚወክሉ ሀገራት አንዷ ማድረግ እንደሚቻል ገልፀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው እንዳሉት÷ ድሬዳዋ ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ፈርጥ ሆነው የሚጠቀሱ ድንቅ ተጫዋቾችና በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ተሳታፊ የነበሩ ክለቦች ያፈራች ከተማ ናት፡፡

ዛሬ ይፋ የተደረገው “ፊፋ ፉትቦል ፎር ስኩል ፕሮጀከት” ድሬዳዋ በዘርፉ ያላትን የቀድሞ ስም ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ያስችላል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.