Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለቦች ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በ6ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ላይ ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ 100 እና 75 ሺህ እንዲቀጡ መወሰኑን የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ በ6ኛ ሣምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲስፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በተጫዋች ደረጃ ቴዎድሮስ በቀለ ከሀምበሪቾ ዱራሜ፣ ተስፋየ መላኩ ከወልቂጤ ከነማ፣ ሞሰስ አዶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ግሩም ሀጎስ ከመቻል በሜዳ ውስጥ ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ የ3 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡

በክለብ ደረጃ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የዕለቱ ዳኞችን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸውና የውሀ መጠጫ ፕላስቲክ ጠርሙስ ወደሜዳ ስለመወርወራቸው ሪፖርት ቀርቧል፡፡

ደጋፊዎቹ በፈፀሟቸው ሁለት ያልተገቡ ድርጊቶች ክለቡ በድምሩ 75 ሺህ ብር እንዲከፍል ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም የራሳቸውን ቡድን ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው እና ለመደባደብ ስለመሞከራቸው ሪፖርት ቀርቧል፡፡

የክለቡ ደጋፊዎች በፈፀሙት ድርጊት እና ከዚህ በፊት ከፈፀሙት ስህተት ሊማሩ ባለመቻላቸው የ100 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡

በተጨማሪም የመቻል እና ወልቂጤ ከተማ አራት ተጫዋቾች፣ የአዳማ ከተማ አምስት ተጫዋቾች እንዲሁም የባህርዳር ከተማ ስምንት ተጫዋቾ በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው መሆኑ ሪፖርት የቀረበባቸው ሲሆን ፥ 5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.