Fana: At a Speed of Life!

ሰውነት እና ጥፍርን እንደ ስዕል ሸራ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ኮሪያዊቷ ዳይን ዩን ሰውነቷን ባልተለመደ መልኩ ለየት ያለ አገልግሎት እያዋለችው ትገኛለች።

ወጣቷ ዳይን መዋቢያ ጥፍሯን ጨምሮ መላ ሰውነቷን እንደ ስዕል ሸራ ተጠቅማ አስደናቂ ስራዎቿን በማቅረብ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆናለች።

የፊቷን ገፅታ ከሚያምር ጥቁር ፀጉሯ ጋር እንዲሁም በጥፍሯ ላይ በተለየ መልኩ የሣለችው ሥዕል በበይነ መረብ ተለቆ የበርካቶች መነጋገሪያ እየሆነ ይገኛል፡፡

ከእግር ጥፍሯ እስከ ራስ ፀጉሯ እያንዳንዱን የሰውነት ክፍሎቿን ተጠቅማ የምትሰራቸው ስራዎች ወጣ ያሉ ናቸው ቢባሉም የበርካቶችን ቀልብ ስበዋል።

የምትሰራቸው ስራዎችም በአብዛኛው ውስጣዊ ስሜቶቿን የሚገልጹ መሆናቸውም ነው የሚነገረው።

ሲ ኤን ኤን በጉዳዩ ላይ ዳይን ዩንን በበይነ-መረብ አግኝቶ ያነጋገራት ሲሆን፥ በቆይታቸው “የሚያምር ሥራ እንደሠራሁ አስባለሁ” ፤ “በርካቶች ግን ጥፍር ላይ የሠራሁትን ሥራ አስፈሪ እንደሆነ ያስባሉ ማለቷን አስነብቧል፡፡

ዳይን አሁን ከደቡብ ኮሪያ ወጥታ ነዋሪነቷን በአሜሪካ አድርጋለች፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ከምትሰራው ስራ ጋር በተገናኘ የተሻለ እንድትንቀሳቀስ እንዳደረጋት ትናገራለች።

የ30 ዓመቷ ዳይን ዩን በደቡብ ኮሪያ ሰዎች ፊታቸውን ቢያዞሩባትም በአሜሪካ ግን አድናቆትን አግኝታለች፡፡

በተለይ በፈረንጆቹ 2016 ላይ ሥራዎቿ የአሜሪካ ብዙኃን መገናኛ መነጋገሪያ መሆናቸውን ተከትሎ የደቡብ ኮሪያውያንም ትኩረት ማግኘት ጀምራለች፡፡

ዳይን የተወለደችበት ሀገር የደቡብ ኮሪያ ሕዝብ ያደነቀው “ሥራዎቼን ሳይሆን በአሜሪካ ትኩረት መሳቤን ነው” ስትል ትገልጻለች፡፡

አሁን ላይ ለዕውነታ የቀረቡ የሚዳሰሱ የሚመስሉ በሰውነቷ ላይ የምትሥላቸው ሥዕሎች ዝናን አትርፈውላታል፡፡

እሷም ከሰውነቷ በተጨማሪ ዕይታዋን በማስፋት በቤት መስኮቶች በሚዳሰሱ ሞዴሎች እና በመሳሰሉት ላይ ሥራዎቿን እያወጣች ነው፡፡

የዓለም ታዋቂ ሙዚቀኞችን ትኩረት አግኝታም ከሃስሊ እና ጀምስ ብሌክ ጋር እየሠራች ነው፡፡

ይህም “ዘኤለን ዲጀነረስ ሾው” በተባለ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ እንድትቀርብ እና ዝናዋ የበለጠ እንዲናኝ ማድረጉ ተነግሯል፡፡

ዳይን ዩን አሁን ለኤስቲ ላውደር ፣ ቢ. ኤም. ደብሊው ፣ አፕል እና አዲዳስ ለተባሉ ዓለም አቀፍ ታዋቂ ኩባንያዎች የማስታወቂያ ሥራዎችን የምትሠራ ዝነኛ ሰው ሆናለች፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.