Fana: At a Speed of Life!

የጋራ ግብረ-ኃይሉ ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ በዕቅድ እየተመራ የፀጥታ ተግባሩን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገሪቱን ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ በሚያስችል ዕቅድ እየተመራ የፀጥታ ተግባሩን እያከናወነ መሆኑን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለጸ።

የጋራ ግብረ-ኃይል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 44ኛው የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።

ዝግጅት አድርጎና ስምሪት ወስዶ ወደ ስራ መግባቱን የገለጸው የጋራ ግብረ-ኃይሉ፤ ወቅቱ የገና እና የጥምቀት በዓላት የሚከበሩበት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚካሄድበት በመሆኑ የሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ በሚያስችል ዕቅድ እየተመራ የፀጥታ ተግባሩን እያከናወነ ይገኛል ብሏል።

ከዚህም ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጭ ለሚኖሩ ለ2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ባቀረቡት ጥሪ መሠረት እንግዶቹ ወደ ሀገራችን መግባት በመጀመራቸው የሀገራችን ሰላምና ፀጥታ በሚገባ ለማረጋገጥ አስተማማኝ የፀጥታ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ሲል ገልጿል።

በሽብርተኞችና በፅንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ የፀጥታ አካላት ባካሄዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን ለኅብረተሰቡ ስጋት የሚፈጥሩ የወንጀል ድርጊቶችን በከፍተኛ ደረጃ በመቆጣጠር ሰላሟ የተረጋገጠ ከተማ ለመፍጠር የተጠናከረ የፀጥታ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጧል።

በቀጣይ በሀገራችን የሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን ጨምሮ ሀይማኖታዊና መንግሥታዊ ሁነቶች በሰላም ተጀምረው በሰላም እንዲጠናቀቁ ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን ሆኖ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ሲልም የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በጉባዔው የሚሳተፉ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን እና ሌሎች እንግዶችን ተቀብላ ስታስተናግድ በተሰጣት ኃላፊነት እና በተጣለባት እምነት ልክ የእንግዶቿን ደህንነት መጠበቅ እና ማረጋገጥ ከፀጥታ አካላቱ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

ይህንኑ የሚመጥን በተግባር የተደገፈ ልምምድና በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የጋራ ግብረ-ኃይሉ በመግለጫው አመልክቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.