Fana: At a Speed of Life!

የዓይን መንሸዋረር ምልክቶችና ህክምናው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓይን መንሸዋረር ማለት የዓይን ጡንቻዎች ሚዛን መሳት ማለት ነው፡፡

የህጻናት የዓይን ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር አዲሱ ወርቁ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ እያንዳንዱ ዓይን ስድስት ጡንቻዎች አሉት ብለዋል፡፡

እነዚህ ጡንቻዎች በመተባበር ሁለቱ ዓይኖች እኩል ወደ አንድ አቅጣጫ ማዞር ስራቸው እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

ይህን ጥምረት አንዱ ከሳተ መንሸዋራር እንደሚያጋጥም ጠቅሰዋል፡፡

የዓይን መንሸዋረር በተፈጥሮ እና ከጊዜ በኋላ ሊያጋጥም የሚችል ችግር ነው። በተፈጥሮ የሚከሰተው መንሸዋረር ከ4ወር በኋላ ጀምሮ ሊታይ የሚችል ሲሆን፥ በህክምና ሊስተካከል የሚችልበት ዕድል አለ።

ከጊዜ በኋላ የሚከሰተው የዓይን መንሸዋረር በመነጽርና በቀዶ ህክምና መስተካከል ይችላል።

በአብዛኛው በኢትዮጵያ የሚከሰተው ወደውስጥ የሚዞር የዓይን መንሸዋረር እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር አዲሱ፥ በሌሎች ሀገራት የሚከሰቱ ወደውጭ የሚዞር የዓይን መንሸዋረር እና ወደላይና ወደታች የሚዞር የዓይን መንሸዋረር እንደሆኑም ነው የገለጹት፡፡

ወደውጭ የሚዞር የዓይን መንሸዋረር ሁለት ዓይነት የህክምና ሂደት አለው፡፡ አንደኛው ህክምና በሦስተኛ ዓመት ዕድሜ ላይ ሁለተኛው ህክምና ደግሞ በሥምተኛ ዓመት ዕድሜ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ሦስት ዓመት ላይ የሚባለው፡- የሰው ልጅ ሲወለድና በሦስት ዓመቱ ያለው የዓይን ኳስ እድገት እኩል አይደለም፡፡

ህጻናት ሲወለዱ 16 ሚሊሜትር አካባቢ መጠን ሲኖረው እስከሦስት ዓመታቸው ግን 23 ሚሊ ሜትር ይደርሳልም ነው ያሉት፡፡

የአንድ ትልቅ ሰው ደግሞ 24 ሚሊሜትር አካባቢ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም ህክምናውን ለማድረግ የዓይን ኳሱ በሦስት ዓመቱ እድገቱን ጨርሷል ተብሎ ስለሚታመን ህክምና ይደረጋል ብለዋል የህክምና ባለሙያው፡፡

በሥምንት ዓመቱ የሚሄድበት ምክንያት ደግሞ የዓይን የእይታ እድገቱ እስከሥምንት ዓመቱ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም በአብዛኛው ወደውጭ የሚዞረው የዓይን መንሸዋረር ህክምና በሥምንት ዓመት ቢሆን እንደሚመረጥም ነው የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.