Fana: At a Speed of Life!

መድሐኒቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት አምራቾችን ለማበረታት ጥረት እየተደረገ ነው – ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መድሐኒቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት አምራቾችን ለማበረታት ብዙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

መድሐኒቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል የጥናት ውጤት በጤና ሚኒስቴር ለሚመራው የመድሐኒት አቅርቦት ሰንሠለት ስትሪንግ ኮሚቴ ቀርቧል፡፡

ጥናቱ የተጠናው ከእንግሊዝ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ማካንዚ ከተባለ ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም ጋር በመተባበር ሲሆን÷ ጥናቱ ላለፋት 4 ወራት ሲሰራ ቆይቶ ውጤቱ እንደቀረበም ተገልጿል፡፡

አብዛኛው መድሐኒቶች ከውጭ ሀገራት ተገዝተው የሚመጡ በመሆኑ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ለማሳደግ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም ይህን ለማሻሻል ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ጥናቱ ሊጠና መቻሉ ተጠቅሷል፡፡

ከውጭ ሀገራት ተገዝተው የሚቀርቡ መድሐኒቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ባሻገር ወደ ውጭ በመላክም ጭምር ኢትዮጵያን በአፍሪካ የመድሐኒት አምራቾች ማዕከል ለማድረግ ለተያዘው አላማ ጥናቱ ግብዓት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡

መድሐኒትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት አምራቾችን ለማበረታት ብዙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ ድርጅት፣ አርማወር ሀንሰን የጥናት ኢንስቲዩት ያሉበት ቡድን ተቋቁሞ ጥናቱ በጥልቀት እንደሚታይ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት እና ለወረርሽኞች ምላሽ ለመስጠት እየተደረጉ ያሉ የመድሐኒት ስርጭቶች ላይ ምክክር ተካሂዷል፡፡

የመድሐኒት እጥረትን ለመፍታት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ላይም ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.