Fana: At a Speed of Life!

የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምንነት፣ መንስኤና መከላከያው

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህፀን ጫፍ ካንሰር ማለት በማህፀን ጫፍ ላይ ያልተለመደ የህዋስ እድገት ሲከሰትና ይህም በመላው የማህፀን ጫፍ አካባቢ ሲዛመት ነው፡፡

ለማህፀን በር ካንሰር ተጋላጭ የሚሆኑት እነማን ናቸው?

ማንኛውም የግብረ ስጋ ግንኙነት ፈጽማ የምታውቅ ሴት ሁሉ ለማህፀን በር ካንሰር የመጋለጥ አጋጣሚ ሊኖራት ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ በለጋነት ዕድሜ (ከ20 ዓመት እድሜ በታች) የግብረ ስጋ ግንኙነት የጀመሩ ሴቶች፣ ከተለያዩ ወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሴቶች፣በተለያዩ ምክንያቶች የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም መዳከም ያጋጠማቸው ሴቶች (ለምሳሌ ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ ያለ) እንዲሁም በአባላዘር በሽታ የተያዙ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡

የማህፀን በር ካንሰር ዋና ዋና ምልክቶች ምንድናቸው?

የማህፀን በር ካንሰር ምንም ዓይነት የሕመም ስሜትና ምልክት ሳያሳይ ከ15 እስከ 20 ዓመት ሊቆይ ይችላል፡፡

በሽታው ከተባባሰ በኋላ ግን ከወር አበባ ወቅት ውጭ የማህጸን ደም መፍሰስ፣ የወር አበባ ጊዜ የተራዘመና ከባድ መሆን፣ የመውለጃ ጊዜ ወይም ዕድሜ ካለፈ በኋላም የደም መፍሰስ ማጋጠም፣ያልተለመደ ወይም ለየት ያለ ጠረን ያለው የብልት ፈሳሽ ፣ድካም፣ የወገብ ህመም፣ ክሳት፣ የሆድ ህመም እና የመሳሰሉት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡

የማህፀን በር ካንሰርን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከል በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ፣ከ20 ዓመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ሴቶች የማህጸን በራቸው ያልዳበረ በመሆኑ በለጋነት ዕድሜ የግብረ ስጋ ግንኙነት ያለመፈጸም፣ኤች ፒ ቪ ክትባትን መከተብ፣አንድ ለአንድ መወሰንና የአባላዘር በሽታን መከላከል ዋነኞቹ የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ዘዴዎች መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የማህፀን ጫፍ ካንሰር የሚያስከትላቸው ጉዳቶችስ ምንድናቸው?

የደም መርጋት፣የደም መፍሰስ፣ፊስቱላ፣የሆድ ድርቀት፣የመሽናት ችግር፣መካንነት፣የውስጣዊ አካል ከጥቅም ውጪ መሆንና የመሳሰሉትን ጉዳቶች በማምጣት የማህፀን በር ካንሰር እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል ህመም ነው፡፡

በዓለም በየዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች በማኅጸን ጫፍ ካንሰር እንደሚያዙ ይገመታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.